የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ስኬታማ በሆነ መንገድ ተከናውኗል - የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) - ኢዜአ አማርኛ
የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ስኬታማ በሆነ መንገድ ተከናውኗል - የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 9/2017(ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ስኬታማ በሆነ መንገድ መከናወኑን የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) አስታወቁ።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያየ1 2ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ከሰኔ 23 እስከ ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በወረቀትና በበይነ መረብ ተሰጥቷል።
የትምህርት ሚኒስትሩ፥ የፈተናውን መጠናቀቅ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ፈተናው ስኬታማ በሆነ መንገድ ተካሂዷል።
ፈተናው በስድስት ዙር የተሰጠ መሆኑን ያወሱት የትምህርት ሚኒስትሩ፤ ከዚህ ቀደም ከተሰጡት ፈተናዎች በተሻለ መልኩ የተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት ከ29 ሺህ በላይ ተፈታኞች በበይነ መረብ መፈተናቸውን ገልጸው፥በ2017 ዓ.ም 134 ሺህ በበይነ መረብ መሰጠቱን ገልጸዋል።
ፈተናው በ139 ፈተና ጣቢያዎች መሰጠቱን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በ40 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መካሄዱን አንስተዋል።
የዘንድሮው ፈተና የታለመለትን ዓላማ ያሳካ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ በዲጂታል የሚሰጠውን ፈተና ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በሚቀጥለው ዓመት በበይነ መረብ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ቁጥር ወደ 50 በመቶ ከፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘንድሮ 23 ነጥብ 2 በመቶ በበይነ መረብ መውሰድ መቻላቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም በትምህርት ቤቶች ኮምፒውተሮችን ተደራሽ የማድረግ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።