በአፋር ክልል በአራት የተለያዩ ቦታዎች አዲስ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ተከስቷል

ሰመራ ፤ ሐምሌ 9/2017(ኢዜአ)፦በአፋር ክልል በአራት የተለያዩ ቦታዎች አዲስ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ መከሰቱን የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የእሳተ ጎመራ ፍንዳታ ክስተቱን ተከትሎ በተለይም በጉብኝት ላይ የነበሩ የውጭ ሀገራት ቱሪስቶችን ትኩረት መሳቡን ቢሮው አስታወቋል።

በክልሉ ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ሃብት ማስተዋወቅና ገበያ ልማት ዳይሬክተር አቶ አብዱ አህመድ፤  ከትናንት ጀምሮ ከዋናው ኤርታሌ በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በአራት የተለያዩ ቦታዎች አዲስ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ተከስቷል ብለዋል።


 

ክስተቱ በቱሪስቶችም ሆነ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አለማድረሱን ጠቅሰው፤ ሁኔታው በተለይም በጉብኝት ላይ ያሉ የውጭ ሀገራት ቱሪስቶችን ቀልብ በእጅጉ ስቧል ብለዋል።

በአካባቢው የሚገኙ ቱሪስቶች በቅርበት ሆነው በአድናቆትና መገረም በትኩረት እየተከታተሉት መሆኑንም ገልጸዋል።


 

የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ከመሬት በታች የሚገኘው የማግማ ግፊት ሲጨምር ወይም የምድር ቅርፊት ስንጥቆችን በመፍጠር አዳዲስ መውጫ መንገዶችን ሲያገኝ የሚከሰት መሆኑን የዘርፉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም