በበጀት ዓመቱ ከ600 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ ከ600 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ ነው

ሀዋሳ ፤ ሐምሌ 9/2017(ኢዜአ):- በአዲሱ በጀት ዓመት ከ600 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላከ ቡና ከ2 ነጥብ 65 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡
በተጀመረው አዲስ በጀት ዓመት ከ600 ሺህ ቶን በላይ ቡና ወደ ውጭ በመላክ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ወደ ውጭ ለመላክ የታቀደው የቡና መጠን ከተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት የ150 ሺህ ቶን ጭማሪ እንዳለው የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ወደውጭ የሚላከው የቡና መጠን በየዓመቱ እያደገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዘርፉ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ አርሶ አደሩ ማሳውን እንዲያድስ፣ ያረጁ የቡና ተክሎችን እንዲጎነድል እንዲሁም ልማቱን በጥራትና በስፋት እንዲያከናውን እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
እንደሀገር የቡና ምርትና ምርታማነት የማሳደግ፣ ጥራትን የማስጠበቅና ግብይትን የማዘመን ሥራዎች ላይ በማተኮር በዘርፉ እየተመዘገቡ ያለውን ውጤቶችን የሚያስቀጥሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
የቡና ጥራትን ለማስጠበቅ አዲስ የኤክስቴንሽን ፓኬጅ ተቀርጾ ወደ ስራ መግባቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ባለስልጣኑ ከክልሎች ጋር በመቀናጀት የአርሶ አደሩን ግንዛቤ የሚያሳድጉ ስልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል ቡና ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ቃሬ በበኩላቸው ከክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ38 ሺህ 500 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡
ከቀረበው ቡናም ከ90 ከመቶ በላይ የሚሆነው ደረጃ 1 እና 2 መሆኑን ጠቁመው በ2018 በጀት ዓመት ከ40 ሺህ 169 ቶን በላይ ቡና ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም የቡና ምርትና ምርታማነት የሚጨምሩ ፓኬጆችን የመተግበር፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በተደራጀ መንገድ የማዘጋጀትና በጥምር ደን የማምረት ሥራው እንደሚጠናከር ገልጸዋል፡፡
በክልሉ የቡና ቴክኖሎጂ መንደሮችን በክላስተር በማደራጀት 18 ሺህ ሄክታር መሬት መልማቱን ጠቁመው በአዲሱ በጀት ዓመትም ይህንን ተግባር የማስፋት ሥራ ይሰራል ብለዋል።