በኦሮሚያ ክልል በቡና ልማት የተገኘውን ውጤት በማስቀጠል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በቡና ልማት የተገኘውን ውጤት በማስቀጠል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ ይሰራል

አዳማ ፤ ሐምሌ 9/2017(ኢዜአ):-በኦሮሚያ ክልል በቡና ልማት የተገኘውን ውጤት በማስፋፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚሰራ የክልሉ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ።
በክልሉ በ2017 በጀት አመት የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች የተገኙ ስኬቶችና አፈፃፀም፣ የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ግምገማ መድረክ ዛሬ በአዳማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ፣ ቡና ለሀገሪቱ የብልጽግና ጉዞ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ይህንን ታሳቢ በማድረግ በክልሉ የቡና ልማትን ለማስፋፋት ባለፉት ስድስት ዓመታት በተደረገው ርብርብ አመርቂ ውጤት ታይቷል ብለዋል።
በተለይ መንግሥት የቡና ምርትና ምርታማነትን በመጨመርና ጥራቱን በማሻሻል በዓለም ገበያ ተወዳዳሪነቱን የበለጠ በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግሩን እውን ለማድረግ በልዩ ትኩረት መሰራቱን ገልጸዋል።
በዚህም መንግስት፣ አርሶ አደሮች፣ ቡና ላኪዎችና ባለድርሻ አካላት ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት በምርታማነትና በገቢ የተሻለ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
በዚህም ህይወቱን በቡና ልማት ላይ የመሰረተው አርሶ አደር ተስፋ ሰጪ ውጤት በማግኘቱ የልማት ተሳትፎውን ይበልጥ ለማጠናከር በዚህ ዓመት ርብርብ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
በዚህ ረገድ ቡና ላኪዎች አርሶ አደሩ ከልፋቱ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆን ድጋፋቸውን ከማጠናከር ባሻገር በቡና ልማት በስፋት እንዲሳተፉ ጠይቀው የክልሉ መንግስትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።
በክልሉ በቡና ልማት ረገድ የተገኘውን ውጤት ዘላቂነቱን ለማስጠበቅ በየደረጃው የሚገኘው አመራር በልዩ ትኩረት እንዲሰራም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በበኩላቸው ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ እንደ ሀገር በቡና ልማት ከፍተኛ ውጤት እየታየ መጥቷል ብለዋል።
የቡና ልማትን ከማስፋፋት ባለፈ በኤክስፖርት ግኝትም ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ውጤት የተመዘገበው ከሁሉም ክልሎች እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት በመቻሉ እንደሆነ አመላክተዋል።
ቡና ለውጭ ገበያ የማቅረቡ ሥራ ለዘመናት በተወሰኑ ላኪዎች ቁጥጥር ስር የነበረበትን ሁኔታ በመቀየር አርሶ አደሩን ጨምሮ አዳዲስ ላኪዎችም እንዲካተቱ አሰራር ተዘርግቷል ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላከው 469 ሺህ ቶን ቡና 2 ነጥብ 65 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውሰው በ2018 በጀት ዓመትም 600 ሺህ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ፣ በክልሉ የቡና ምርታማነትና ጥራት ለማሳደግ የተለያዩ ኢኒሼቲቮች ተቀርፀው በተደረገው ርብርብ አመርቂ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
በክልሉ ባለፉት አምስት አመታት የቡና ልማትን ለማስፋፋት በተደረገው ርብርብ በየአመቱ የሚተከለውን የቡና ችግኝ ብዛት በ23 በመቶ ማሳደግ መቻሉን አስታውቀዋል።
በዚህም የክልሉን አመታዊ የቡና ምርት ከ4 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 15 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ማሳደግ መቻሉን አመልክተዋል።
ከዚህም ባለፈ በክልሉ ከ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሔክታር በላይ መሬት ላይ ቡና እየለማ መሆኑን ጠቅሰው የቡና ልማት ምርታማነትን በሔክታር ከ6 ነጥብ 5 ኩንታል ወደ 9 ኩንታል ማሳደግ እንደታቻለም አውስተዋል።