በአፍሪካ የታዳጊ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚሳተፉባቸው አምስት የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2017(ኢዜአ):- በናይጄሪያ አቡካታ የሚካሄደው ሶስተኛው የአፍሪካ ከ18 ዓመት እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ይጀመራል።

በሻምፒዮናው ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ43 ሀገራት የተወጣጡ 937 አትሌቶች ይሳተፋሉ።

በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያ 30 ወንድ እና 27 ሴቶች በድምሩ 57 አትሌቶችን ታሳትፋለች። አጠቃላይ 69 የአትሌቲክስ ልዑክ ወደ ስፍራው አምርቷል። 

በሻምፒዮናው መክፈቻ ቀን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው አምስት የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ።

በ1500 ሜትር ሴት ከ18 ዓመት በታች ፍፃሜ ኤልሳቤጥ አማረ፣ ደስታ ታደሰ እና ቦንቱ ዳንኤል ይሳተፋሉ። 

ምሽት 1 ሰዓት ከ35 ላይ ስሉስ ዝላይ ሴት ከ20 ዓመት በታች ፍፃሜ ኛቾክ ቾል ትወዳደራለች።

አትሌት ሳሙኤል ገብረሃዋርያ እና አትሌት አብርሃም ገብረእግዚአብሔር ምሽት 1 ሰዓት ከ40 ላይ በሚካሄደው 1500 ሜትር ወንድ ከ18 ዓመት በታች ፍፃሜ ላይ ይሳተፋሉ።

ምሽት 3 ሰዓት ከ10 ላይ በ3000 ሜትር ሴት ከ20 ዓመት በታች ፍፃሜ ቤተልሄም ጥላሁን ትርሐስ ገብረህይወት እና ውድነሽ አለሙ የሚወዳደሩ ይሆናል።

አትሌት ንብረት ክንዴ ምሽት 3 ሰዓት ከ25 በ10000 ሜትር ወንድ ከ20 ዓመት በታች ፍፃሜ ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ ይወዳደራል። 

ከፍጻሜ ውድድሮቹ በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የማጣሪያ ውድድሮች ይካሄዳሉ።

በሻምፒዮናው ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች የተመረጡት በድሬዳዋ ከተማ በግንቦት ወር 2017 ዓ.ም በተካሄደው 13ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና 4ኛው የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና  ባስመዘገቡት ውጤት መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል። 

ሶስተኛው የአፍሪካ ከ18 ዓመት እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና እስከ ሐምሌ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም