ሰራዊቱ አረንጓዴ ዐሻራን ባህል የማድረግ ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል - ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2017(ኢዜአ)፦ ሰራዊቱ በመኖሪያ ካምፕ እና በግዳጅ ቀጣናው አረንጓዴ ዐሻራን ባህል የማድረግ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ማስጀመራቸው ይታወቃል።


 

የመከላከያ ሰራዊት የዘንድሮ የአረንጓዴ ዐሻራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በመከላከያ ሚኒስቴር ጠቅላይ መምሪያ ዋና ግቢ ተካሂዷል።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ጄኔራል መኮንኖችና የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ተገኝተዋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ሰራዊቱ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሮች ከፍተኛ ተሳትፎ አድርጓል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር እንደሀገር ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የደን ሽፋንን በማሳደግ፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ውጤት እያመጣ ነው ብለዋል።

የመከላከያ ሰራዊቱም የበኩሉን ሚና በመወጣት ዐሻራውን እያኖረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

የዘንድሮ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ከዛሬ ጀምሮ ሰራዊቱ በያለበት የግዳጅ ቀጣና እና በመኖሪያ ካምፖች ጭምር ችግኝ በመትከል አረንጓዴ ዐሻራን ባህል የማድረግ ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ቶማስ ቱት በበኩላቸው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከተሰጠው ግዳጅ ጎን ለጎን በአካባቢ ጥበቃ ላይ በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል ብለዋል።

በዘንድሮ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በመከላከያ ሰራዊት ከ18 ሚሊየን በላይ ሀገር በቀል እና ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች እንደሚተከሉም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም