የሴቶች አውሮፓ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶች አውሮፓ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2017 (ኢዜአ):- በ14ኛው የሴቶች የአውሮፓ ዋንጫ የመጀመሪያው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ በአየርላንድ እና ጣልያን መካከል ዛሬ ይደረጋል።
የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ምሽት 4 ሰዓት በጄኔቭ ስታዲየም ይካሄዳል።
የሁለት ጊዜ የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊዋ ኖርዌይ በምድብ አንድ ያደረገቻቸውን ሶስት ጨዋታዎች በማሸነፍ በዘጠኝ ነጥብ የምድቧ መሪ ሆና አልፋለች።
ተጋጣሚዋ ጣልያን በምድብ ሁለት በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅላለች።
ሁለቱ ቡድኖች እስከ አሁን በውድድር እና ወዳጅነት ጨዋታዎች 12 ጊዜ እርስ በእርስ ተገናኝተዋል። ኖርዌይ 7 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ስትይዝ ጣልያን 2 ጊዜ ድል ቀንቷታል። ሁለት ጊዜ አቻ ወጥተዋል።
ኖርዌይ በጨዋታዎቹ 21 ግቦችን ስታስቆጥር ጣልያን 14 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፋለች።
ሁለቱ ቡድኖች በተገናኙባቸው ጨዋታዎች በአንድ ጨዋታ በአማካይ ከሁለት ግቦች በላይ ይቆጠራል።
ሀገራቱ እ.አ.አ በ2024 ለ14ኛው የሴቶች አውሮፓ ዋንጫ ለማለፍ በምድብ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል (1-1 እና 0-0)።
ኖርዌይ እ.አ.አ 1987 እና 1993 የሴቶች አውሮፓ ዋንጫን አሸንፋለች። በ1987 ዋንጫውን ያነሳቸው አዘጋጇ ሀገር ጣልያንን በማሸነፍ ነበር።
ጣልያን እ.አ.አ 1993 እና 1997 ለፍጻሜ ደርሳ በቅደም ተከተል በኖርዌይ እና ጀርመን ተሸንፋ ዋንጫውን አጥታለች።
ኖርዌይ የሩብ ፍጻሜን ጨዋታ የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት አግኝታለች።
የጨዋታው አሸናፊ በግማሽ ፍጻሜው ከእንግሊዝ እና ስዊድን አሸናፊ ጋር ይገናኛል።
በስዊዘርላንድ እየተካሄደ የሚገኘው 14ኛው የሴቶች የአውሮፓ ዋንጫ ዛሬ 15ኛ ቀኑን ይዟል።