የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አቡዳቢ ዕለታዊ አዲስ የመንገደኞች በረራ ጀመረ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አቡዳቢ ከተማ በየቀኑ የሚደረግ አዲስ የመንገደኞች በረራ ጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የቦርድ ሊቀመንበር ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው የአየር መንገዱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ በኢትዮጵያ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ ሀማድ ፋሪድና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የቦርድ ሊቀመንበር ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ በዚሁ ወቅት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለ80 አመታት ገደማ አፍሪካን ከመላው ዓለም እያስተሳሰረ የቆየ ግዙፍ የአቪዬሽን ማዕከል መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዛሬው እለትም ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አቡዳቢ የተጀመረው አዲስ የበረራ መስመር የሁለቱን ሀገራት ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር እንደሚሆን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ አየር መንገዱ ወደ አቡዳቢ የጀመረው የመንገደኞች የበረራ አገልግሎት በአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ መካከል ያለውን ትስስር የሚያጎለብት ይሆናል ብለዋል።

አየር መንገዱ እ.አ.አ ከ1979 ጀምሮ ወደ ዱባይ የመንገደኞች አገልግሎት በመጀመር ዛሬ ላይ በሳምንት 21 ጊዜ በረራ ያደርጋል ነው ያሉት።

በዛሬው እለትም አየር መንገዱ ከረጅም ጊዜ በኋላ በአዲስ መልክ ወደ አቡዳቢ አገልግሎት መጀመሩ በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ተደራሽነት የሚያሰፋ ይሆናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ምክትል ሚሲዮን መሪ ሀማድ ፋሪድ፤ የበረራው መጀመር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ፣ ቱሪዝም እና የባህል ልውውጥ እንደሚያሳድግ ጠቁመዋል።

አየር መንገዱ ከአንድ ወር በፊት ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሻርጃ በሳምንት አራት ጊዜ የሚደረግ አዲስ በረራ መጀመሩ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም