ክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሁሉም ዘርፎች ስኬቶች ተመዝግበዋል - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 8/2017(ኢዜአ)፡- በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሁሉም ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ ውጤቶች መመዝገባቸውን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ፡፡

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ ሲሆን በዛሬው ውሎው የክልሉን መንግስት የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2018 ዕቅድ በመገምገም አፅድቋል፡፡


 

ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፤ ከመድረኩ በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ በሁሉም ዘርፎች በብዙ መመዘኛዎች ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በምጣኔ ኃብት፣ በግብርና፣ በከተማ ልማት እንዲሁም የኢንዱስትሪና ሌሎች መስኮች የተገኙ ውጤቶችን በመዘርዘር በእንስሳት ሃብት ልማት፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በውሃ ልማትና ተደራሽነት፣ በትምህርትና ጤና ዘርፎች በርካታ ስራዎች መሰራታቸውንና ውጤቶችም መገኘታቸውን አብራርተዋል።

በክልሉ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ በከፍተኛ ትኩረት እየተመራ ያለ መሆኑን ጠቁመው በዚህ ረገድ እንደ ሀገር የተያዘውን ግብ ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ረገድም በጥናት ላይ በመመስረት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አንስተው በቀጣይ በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

‎ምክር ቤቱ ማምሻውን የክልሉን የ2018 ዓ.ም በጀት 32 ነጥብ 82 ቢሊዮን ብር ያፀደቀ ሲሆን በጀቱም ‎ከክልሉ የውስጥ ገቢ፣ ከፌደራል መንግስት በሚሰጥ ድጎማና ከሌሎች የገቢ ምንጮች የሚሸፈን መሆኑ ተገልጿል።

የምክር ቤቱ ጉባኤ ነገም ቀጥሎ የሚውል ሲሆን በቀሪ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት ውሳኔዎችን ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም