የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤቶች ተገኝተውበታል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2017(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤቶች የተገኙበት መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ማስጀመራቸው ይታወቃል።

በዚህም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ የቤተ መንግሥት አስተዳደር እና የኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን አመራርና ሠራተኞች በመልካሳ ቤተመንግሥት የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አከናውነዋል።


 

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከጀመረ ወዲህ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከነበረበት መመናመን ወጥቶ እድገት አስመዝግቧል።


 

በመርሐ ግብሩ የሚተከሉ ችግኞች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው በመሆኑ የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባሻገር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤቶች እየተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የደን ሀብት መመናመን፣ የአፈር መሸርሸርና ድርቅን ለመሳሰሉ አደጋዎች የመጋለጥ ችግሮች ሲያጋጥሙ እንደነበር አንስተዋል።


 

ይህንን ለመቅረፍም በተከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብሩ ችግሮቹን ለመቅረፍ ያስቻሉ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የቤተ-መንግሥት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ምትኩ ዴሬሳ እንዳሉት መርሀ ግብሩ ሀገሪቱን አረንጓዴ ገጽታ በማላበስ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አቅም እንዲያድግ እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

አረንጓዴ ዐሻራ የምግብ ዋስትናን፣ የውሃ ሃብትንና የብዝሃ ህይወት ጥበቃን በማረጋገጥ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ ናቸው።


 

በዘንድሮው አመትም "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለመትከል ታቅዶ እየተተገበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም