በዞኑ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የአካባቢውን ሥነ ምህዳር የሚያስጠብቁና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ችግኞች እየተተከሉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የአካባቢውን ሥነ ምህዳር የሚያስጠብቁና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ችግኞች እየተተከሉ ነው

አዳማ፤ ሐምሌ 8/2017(ኢዜአ)፦ በምስራቅ ሸዋ ዞን በአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የአካባቢውን ሥነ ምህዳር የሚያስጠብቁ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ችግኞች በስፋት እየተተከሉ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አብነት ዘገየ እንዳሉት ከሚተከሉት ችግኞች ውስጥ 35 በመቶ የሚሆኑት ለምግብነት የሚያገለግሉ እንደ አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ፓፓዬ፣ ብርቱካንና ሌሎች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
ዘንድሮ በዞኑ ለሚካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በዞኑ በሚገኙ 11 ወረዳዎች ውስጥ ከ59ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተለይቷል ብለዋል።
በተከላ መርሐ ግብሩም አርሶ አደሮች፣ ወጣቶች እንዲሁም ሌሎችም በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ገልጸው፤ ለተከላው በጉድጓድ ቁፋሮና በሌሎችም ዝግጅቶች እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ የሚተከሉት ችግኞች የአካባቢውን ሥነ ምህዳር ከማስጠበቅና ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑንም አብራርተዋል።
ዞኑ በመትከል ላይ ብቻ ሳይሆን ነባር የደን ቦታዎችን ከልሎ በመጠበቅና በመንከባከብ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከተሳተፉ የዞኑ ነዋሪዎች መካከል የቦሰት ወረዳ ነዋሪዎች ባለፉት ዓመታት ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ጸድቀው አገልግሎት እንዲሰጡ፣ ጉዳት እንዳይደርስባቸው በመጠበቅ፣ በመኮትኮትና በመንከባከብ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም የዞኑ የደን ሽፋንን ከፍ ለማድረግ የተከላ ቦታዎችን ከመከለል በተጨማሪ የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ ጥበቃ እያደረጉ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በዚህ ዓመትም የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ በችግኝ ተከላው የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።