ህብረተሰቡ በአረንጓዴ አሻራ ለሚተከሉ ችግኞች ጽድቀት ተገቢውን ትኩረት ሊሰጥ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2017 (ኢዜአ)፦ህብረተሰቡ በአረንጓዴ አሻራ የነቃ ተሳትፎን በማጠናከር ለሚተከሉ ችግኞች ጽድቀት ተገቢውን እንክብካቤ ሊያደርግ እንደሚገባ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት እና ሌሎች ተቋማት "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በእንጦጦ ፓርክ አካባቢ አካሂደዋል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፤ የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ መጠበቅ ባለመቻላችን ለልዩ ልዩ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ተጋላጭ ሆነን ቆይተናል ብለዋል። 

የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ለመቋቋም መንግስት ባለፉት ሰባት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርን ቀጣይነት ባለው መልኩ እየተገበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

መርሀ ግብሩ ዜጎችን ለጋራ ዓላማ በንቃት ያሳተፈ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም ጉልህ ስኬቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።

በቀጣይም ዜጎች በአረንጓዴ አሻራ የሚያሳዩትን የነቃ ተሳትፎ በማጠናከር ችግኝ ከመትከል ባለፈ ለፅጽቀትም ተገቢውን ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽነር ይመር ከበደ በበኩላቸው፤ አረንጓዴ አሻራ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገርን የምንገነባበት ትልቅ ተነሳሽነት ነው ብለዋል። 

በመሆኑም ሁላችንም ለችግኝ ተከላ እና እንክብካቤ የምናደርገውን ተሳትፎ አጠናክረን መቀጠል አለብን ነው ያሉት።


 


 

የአዲስ አበባ ሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ ንጉሴ፤ በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ለፍሬ እንዲበቁ እንሰራለን ብለዋል።


 

በእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የየካ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ኒቆዲሞስ ቡቼ በበኩላቸው፤ በተፈጥሯዊ አደጋዎች ሳቢያ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመከላከል አረንጓዴ አሻራን ባህል ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም