ኢትዮጵያ በሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ የአረንጓዴ ልማት ስኬታማ ተሞክሮዋን ታቀርባለች - የፕላንና ልማት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ የአረንጓዴ ልማት ስኬታማ ተሞክሮዋን ታቀርባለች - የፕላንና ልማት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ከማስተናገድ ባሻገር የአረንጓዴ ልማት ስኬታማ ተሞክሮዋን እንደምታቀርብ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ገለጹ።
ጉባኤው ለማስተናገድም ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሕብረት ጋር በመተባበር በጳጉሜ ወር የምታስተናግደውን ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባዔ ዝግጅት በማስመልከት ከዓለም አቀፍ አጋር ተቋማትና ከሲቪክ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን፥ አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ በመንስኤነት ደረጃ ያላት አስተዋፅኦ ዝቅተኛ ቢሆንም ከፍተኛ ጉዳትን እያስተናገደች መሆኑን ገልጸዋል።
ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የበሽታ መስፋፋት፣ የሰደድ እሳት እና ሌሎች ችግሮች በአየር ንብረት ለውጡ ምክንያት አህጉሪቱን ሰለባ እያደረጉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
አደጋ ለመቀልበስና ተፅዕኖን ለመቋቋም በአፍሪካ ደረጃ የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ እና የህግ ማእቀፍ አዘጋጅታ ተጨባጭ እርምጃ እየወሰደች መሆኑን ገልጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዓለም ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋን ለመቀልበስ ተግባራዊና ውጤታማ የሆነ ግዙፍ ተነሳሽነት ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንት እና በትራንስፖርት ዘርፍ ጠንካራ ስራ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቀልበስ እየተወሰዱ ያሉ ሀገር በቀል መንገዶች የሚጎለብቱበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ያደጉ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚመጣውን አደጋ ለመቅረፍ የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ቢስማሙም፥ ባለፉት አስር ዓመታት የተገኘው የገንዘብ መጠን ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
የጉባኤው ዓላማም እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በተስፋፋ እና በተሻለ መንገድ እንዲፈጸሙ ማስቻል መሆኑን አመላክተዋል።
መድረኩ በሀገራት መሪዎች ደረጃ ልዩ ልዩ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት መሆኑን ጠቅሰው፥ እስከ 25 ሺህ የሚደርሱ እንግዶች በዚህ ጉባኤ እንደሚታደሙ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን የመሪነት ሚና የምታጠናክርበት እንዲሁም ተሞክሮዎቿን የምታካፍልበት መሆኑን ገልጸዋል።
ጉባኤው እያንዣበበ ያለውን አደጋ ለመቀልበስ ሀገራት ዳግም ቁርጠኝነታቸውን የሚያረጋግጡበት መሆኑን በማንሳት፥ ኢትዮጵያ ለጉባኤው ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም ዓለም አቀፍ ፋውንዴሽኖች፣ ለጋሽ ተቋማትና የሲቪክ ማህበረሰብ ተወካዮች የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የአየር ንብረት ፋይናንሲንግ ከፍተኛ አማካሪ ምስጋናው እያሱ ከአጋር አካላት ጋር በርካታ ስራዎች እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
እንዲሁም አጋር አካላት ድጋፍ በማድረግ ለጉባኤው ስኬት በጋራ እንስራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥ አደጋን ለመቀልበስ ወሳኝ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት መሆኑን ተናግረዋል።
ለጉባኤው ስኬትም የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት እና ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።