የከተማው የኮሪደር ልማት የሥራ እድል እና ከዘርፉ እውቀት እንድናገኝ አስችሎናል-ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
የከተማው የኮሪደር ልማት የሥራ እድል እና ከዘርፉ እውቀት እንድናገኝ አስችሎናል-ወጣቶች

ደሴ ፤ ሐምሌ 8/2017(ኢዜአ)፡-የደሴ ከተማ የኮሪደር ልማት የሥራ እድል እና ከዘርፉ የሥራ ሂደት እውቀት እንዲያገኙ ያስቻላቸው መሆኑን የከተማው ወጣቶች ገለጹ።
የኮሪደር ልማቱ በተያዘለት ጊዜ እና በጥራት እንዲጠናቀቅ በርካታ ዜጎችን ወደ ሥራ በማስገባት ሥራው እንዲፋጠን እየተደረገ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ገልጿል።
በልማቱ ከተሰማሩት ወጣቶች መካከል ብርሃን አስናቀ በሰጠው አስተያየት በኮሪደር ልማቱ የግንባታ ዘርፍ የሥራ እድል ተፈጥሮለት ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል።
በዚህም ደስተኛ እንደሆነ ጠቅሶ፤ በግንባታው ሂደትም የእውቀት ሽግግር ማድረግ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው ገልጿል።
በግንባታ ሥራ ካናል እና የድጋፍ ግንብ ከመስራት ባለፈ በቴራዞ ማንጠፍ፣ በእግረኛና በብስክሌት መንገድና በሌሎችም ቀለም መቀባትና ተዛማጅ ሙያዎችን ከሌሎች ባለሙያዎች ልምድ መውሰድ ችያለሁ ነው ያለው።
ሌላው ወጣት መጋቢ ባዬ በበኩሉ ፤ በኮሪደር ልማቱ የሥራ እድል በማግኘቱ ከቤተሰብ ጠባቂነት ከመላቀቅ ባለፈ የእውቀት ሽግግር በማድረግ ሌሎችንም አማራጭ ሙያዎች እንድንለምድ አስችሎናል ብሏል።
በዚህም ከረዳት ቴራዞ አንጣፊነት ወደ ሙሉ ባለሙያነት ማደግ በመቻሉ መደሰቱን ጠቁሞ፤ ሌሎችንም የኮንስትራክሽን ሙያዎች መልመድና መማር ችያለሁ ሲል ገለጿል።
የኮሪደር ልማቱ በተያዘለት ጊዜ በጥራት እንዲጠናቀቅ በምሽት ጭምር በመስራት የድርሻዬን እየተወጣሁ ነው ያለው ወጣቱ፤ ለከተማችን መዋብና ማማር አሻራዬን ማስቀመጥ በመቻሌም እድለኛ ነኝ ብሏል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ አበበ ፤ የኮሪደር ልማቱን በጥራትና ፍጥነት ለማጠናቀቅ በሶስት ተቋራጮች በርካታ የሰው ሃይል ተመድቦ እንዲፈጥን እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም ለሁለት ሺህ 144 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን ጠቁመው፤ የእውቅት ሽግግርም እያደረጉ የሥራ ባህል እንዲቀየር አድርጓል፣ ለሌሎች ፕሮጀክቶችም ልምድ የሚሆን ነው ብለዋል።
ቀጣዩን ትውልድ ታሳቢ ተደርጎ እየተሰራ ባለው የኮሪደር ልማት የከተማውን መልካም ገጽታ ይበልጥ በማጉላት ለነዋሪዎች ምቹና ተስማሚ ከማድረግ ባለፈ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም መዳረሻም መደላድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
በኮሪደር ልማቱ እየተሰራ ካለው ሁለት ኪሎ ሜትር መንገድ ውስጥ ከአንድ ነጥብ 36 ኪሎ ሜትር የሚበልጠው የአስፓልት፣ የብስክሌትና የእግረኛ መንገዶች ተጠናቀው የስማርት ፖል ተከላ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
ቀሪውም ሥራው በፍጥነት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።