ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ፈጥኖ መቅረቡ የእርሻ ስራችንን በወቅቱ እንድናከናውን አስችሎናል-አርሶ አደሮች

 

ሰቆጣ፤ሐምሌ 8/2017(ኢዜአ)፡- ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ፈጥኖ መቅረብ በመቻሉ የእርሻ ስራቸውን በወቅቱ ማከናወን እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡ አርሶ አደሮች ገለጹ።

በብሔረሰብ አስተዳደሩ በምርት ዘመኑ 120 ሺህ 638 ሄክታር መሬትን በተለያየ የሰብል ዘር ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የአስተዳደሩ ግብርና መምሪያ አመልክቷል።

በሰቆጣ ወረዳ የሳይዳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ደባሽ አስፋው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ግማሽ ሄክታር የእርሻ መሬታቸውን ማዳበሪያን በመጠቀም ስንዴን በመስመር ዘርተዋል።


 

ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ፈጥኖ መቅረብ በመቻሉ የእርሻ ስራችንን በወቅቱ እንድናከናውን አስችሎናል ያሉት አርሶ አደሩ፤ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በመሆንም ስንዴን በኩታ ገጠም መዝራት መቻላቸውን አንስተዋል።

በማሳቸውን ዳርቻ ላይም እርጥበትን ማቀብ የሚችል ጉድጓድ እንደሚቆፍሩ ነው የተናገሩት።

አርሶ አደር ወርቁ አለሙ በበኩላቸው፥ በግማሽ ሄክታር ማሳቸው ስንዴን በመስመር መዝራታቸውን ተናግረዋል።


 

ባለፈው የምርት ዘመን ሰብልን ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በመጠቀም መዝራት በመቻላችን ምርታማነት እንዲያድግ አስችሏል ያሉት አርሶ አደር ወርቁ፤ አሁንም በኩታ ገጠም አስተራረስ ስንዴን በመስመር መዝራታቸው የተሻለ ውጤት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ፈጥኖ መቅረብ በመቻሉ ደግሞ የእርሻ ስራቸውን ፈጥነው ወደ ስራ እንዲገቡ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል።

በሰቆጣ ወረዳ እስካሁን 23 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያየ የሰብል ዘር ተሸፍኗል ያሉት ደግሞ የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ታምሩ አብርሃ ናቸው።


 

በዘር ከተሸፈነው የእርሻ መሬት ውስጥም 1 ሺህ 600 ሄክታር መሬት በስንዴ፣ጤፍ ፣ማሽላና እንቁ ዳጉሳ የሰብል ዘር በኩታ ገጠም እርሻ ተሸፍኗል ብለዋል።

የአርሶ አደሩ ሰብልን በመስመር መዝራት ብሎም በኩታ ገጠም የመሸፈን ልምድ እያደገ መምጣቱንም ገልጸዋል።

የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ በበኩላቸው፤በምርት ዘመኑ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መመቻቸቱን ተናግረዋል።

ይህም 19ሺህ 385 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና 7 ሺህ 546 ኩንታል መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሃላፊው እንዳሉት፥በ2017/2018 ምርት ዘመን መታረስ ከሚችለው 120 ሺህ 638 ሄክታር መሬት በሰብል ዘር ለማልማት በእቅድ ከተያዘው ውስጥ 35 ሺህ ሄክታር ያህሉ በዘር ተሸፍኗል።

በምርት ዘመኑ ከሚለማው መሬት 4 ሺህ 772 ሄክታር መሬት በስንዴ፣ጤፍ፣ማሽላና እንቁ ዳጉሳ የሰብል ዘር በኩታ ገጠም ለመሸፈን ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም