ደቡብ አፍሪካ፣ ጋና፣ ማሊ እና ሴኔጋል ለሩብ ፍጻሜ አለፉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2017(ኢዜአ)፦ በ13ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ሶስት የመጨረሻ ጨዋታዎች ትናንት ማምሻውን ተደርገዋል።

በሆነር ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ደቡብ አፍሪካ ማሊን 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፋለች።

ሌቦጋንግ ራማሌፔ፣ አምበሏ ሬፊሎ ጄን፣ ሂልዳህ ማጋአ እና ሮኔል ዶኔሊ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ውጤቱን ተከትሎ የወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት ደቡብ አፍሪካ በሰባት ነጥብ ምድቧን በመሪነት በማጠናቀቅ ለሩብ ፍጻሜ አልፋለች።

ማሊ በአራት ነጥብ ሶስተኛ በመሆን በምርጥ ሶስተኝነት ወደ ሩብ ፍጻሜ ገብታለች።

ያሲን ምራቤት በመጀመሪያ አጋማሽ ጭማሪ ደቂቃዎች ላይ በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠረችው ግብ ቡድኑን ባለድል አድርጋለች።

በዚሁ ምድብ ትናንት በቤርካኔ ሙኒሲፓል ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ጋና ታንዛኒያን 4 ለ 1 አሸንፋለች።

ፕሪንሴላ አዱቢ፣ ኢቭሊን ባዱ እና ቻንቴሌ ቦዬ-ሎርካህ በጨዋታ እንዲሁም አሊስ ኩሲ በፍጹም ቅጣት ምት የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ስቱማይ አቱማኒ ለታንዛንያ የማስተዛዘኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፋለች። 

ጋና በአራት ነጥብ ማሊን በግብ ክፍያ በመብለጥ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅላለች።

ውጤቶቹን ተከትሎ በምድብ አንድ በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ሴኔጋል ምርጥ ሶስተኛ በመሆን ሩብ ፍጻሜ መግባት ችላለች።

ሴኔጋል ስምንት ውስጥ የገባችው በምድብ ሁለት በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችውን ቦትስዋናን በግብ ክፍያ መብለጧን ተከትሎ ነው።

የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ሐምሌ 11 እና 12 ቀን 2017 ዓ.ም ይደረጋሉ።

ደቡብ አፍሪካ ከሴኔጋል፣ ናይጄሪያ ከዛምቢያ፣ አዘጋጇ ሞሮኮ ከማሊ እና አልጄሪያ ከጋና በሩብ ፍጻሜው ይገናኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም