የሀገር ውስጥ ምርቶችን መጠቀምን ሁሉም ባህል ማድረግ አለበት - የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር ውስጥ ምርቶችን መጠቀምን ሁሉም ባህል ማድረግ አለበት - የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 7/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የንግድ ስርዓትን በማሳለጥ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባህልን ማጎልበት እንደሚገባ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር) ገለጹ ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ያዘጋጀው 2ኛው ከተማ አቀፍ የኢትዮጵያን ይግዙ የንግድ ሳምንት ኤግዚቢሽንና ባዛር ተከፍቷል።
ኤግዚቢሽንና ባዛሩ "የኢትዮጵያ ምርት ለብልፅግና" በሚል መሪ ሀሳብ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሀምሌ 11/2017 ድረስ በአዲስ አበባ ኢግዚቪሽን ማዕከል ይካሄዳል።
በመርሃ-ግብሩ መክፍቻ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ ጃንጥራር አባይ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ሃቢባ ሲራጅ እና ሌሎችም ታድመዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ 2ኛው ከተማ አቀፍ የኢትዮጵያን ይግዙ የንግድ ሳምንት ኢግዚቢሽንና ባዛር በኢትዮጵያ የሚመረቱ ምርቶችና አገልግሎቶችን የመጠቀም ባህል ለማጎልበት ነው።
የኢትዮጵያን ይግዙ የንግድ ሳምንት ንቅናቄ የሀገሪቱን የንግድ ስርዓት ለማዘመን፣ ምርትና አገልግሎቶችን ተደራሽነት ለማጎልበት ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል።
የንግድ ሳምንቱ የአገር ውስጥ ምርቶችና አገልግሎቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በመሸጥና በመግዛት በኩል ለማህበረሰብ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
የንግዱ ማህበረሰብም የንግድ ፍቃድ አውጥቶ በህጋዊ መንገድ በመስራት የዘርፉ ኢንቨስትመንት እንዲሻሻልና በዘመናዊ አሰራር እንዲካሄድ የራሱን እገዛ ሊያደርግ እንደሚገባውም ነው የገለጹት።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው በከተማዋ የሚደረጉ የንግድ እንቅስቃሴዎች ለኢኮኖሚ እድገቱ ትልቅ ድርሻ እንደሚያበርክቱም ተናግረዋል።
ኢግዚቢሽንና ባዛሩ አምራቾችንና ሸማቾችን በቀጥታ በማገናኘት ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገበያዩ ለማደረግ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ፤ ከተማ አስተዳደሩ የነዋሪውን የኑሮ ጫና ለማቃለል በከተማ ደረጃ ግብር ኃይል በማቋቋም እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎቶች ለማህበረሰቡ እንዲደርሱ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢግዝብሽንና ባዛሩ ላይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት እንዳሉት ምርቶቻቸውን በዝግጅቱ ላይ በማቅረባቸው የተሻለ የንግድ ትስስር ለመፍጠር እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
ምርቶቻቸውን ካቀረቡት መካከልም አቶ ኤልያስ አስቻለው፤ መንግስት መሰል ባዛሮችን ማዘጋጀቱ ለምርቶቻቸው ምቹ ገበያን ከመፍጠር ባሻገር በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።
ቀደም ብሎ በተካሄደው ኢግዚብሽንና ባዛር ላይ በመሳተፍ የገበያ ትስስርን በመፍጠር ምርቶቻቸውን በተሻለ መልኩ ለመሸጥ ምቹ አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው የጠቀሱት ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ትእግስት ተገኝ ናቸው ።