ግብርን በቴሌ ብር መክፈል ጊዜና እንግልትን ከማስቀረት ባለፈ ሀገራዊ ግዴታችንን በወቅቱ ለመወጣት እያገዘን ነው-በሲዳማ ክልል ግብር ከፋዮች

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 7/2017 (ኢዜአ)፦ ግብርን በቴሌ ብር መክፈል ጊዜያቸውን ከመቆጠብና እንግልትን ከማስቀረት ባለፈ ሀገራዊ ግዴታቸውን በወቅቱ ለመወጣት እያገዛቸው መሆኑን የሲዳማ ክልል ግብር ከፋዮች ገለጹ።

የሲዳማ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን በበኩሉ በሰባት ቀናት ውስጥ በክልሉ ከሚገኙ የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ከ220 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ አሰራር መዘርጋቱን አስታውቋል።

በሲዳማ ክልል ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች በቴክኖሎጂ ታግዘው በቴሌ ብር ሃላፊነታቸውን እየተወጡ ሲሆን ዘመናዊ አሰራሩ ጊዜንና እንግልትን ከመቀነስ ባለፈ ግብራቸውን በወቅቱ በመክፈል ሀገራዊ ግዴታቸውን ለመወጣት  እያገዛቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል በክልሉ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ቦርጂ በማማከር አገልግሎት ከሚያገኙት ገቢ የሚጠበቅባቸውን ግብር በቴሌ ብር መክፈላቸው ጊዜያቸውን እንደቆጠበላቸው ገልጸዋል።


 

ግብርን በወቅቱ መክፈል መንግስት ለሚያከናውነው የልማት ሥራ አጋዥ መሆኑን ጠቁመው፣ የግብር አሰባሰቡ መዘመኑ ግብር ከፋዩ በወቅቱ የሚጠበቅበትን ለመወጣት እያስቻለው መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ይርጋለም ከተማ የሚኖረት አቶ ምትኩ ጸጋዬ በበኩላቸው በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር መዘርጋቱ ግብራቸውን በቴሌ ብር ለመክፈልና ጊዜያቸውን ለመቆጠብ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡


 

ግብር ለሃገር እድገት የሚኖረው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ምትኩ የሚጠበቅባቸውን ግብር በታማኝነት እንደከፈሉና ሌሎችም ሃላፊነታቸውን በወቅቱ መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታና ለልማት የሚደረግ አስተዋጽኦ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በክልሉ የወንዶገነት ከተማ ነዋሪው አቶ ማሞ ቱላ ናቸው። 


 

በሚኖሩበት ከተማ እየተከናወነ ያለው ፈጣን የልማት እንቅስቃሴ ግዴታቸውን በወቅቱ እንዲከፍሉ ያነሳሳቸው መሆኑን ተናግረው፣ "አገልግሎቱ በቴሌ ብር መታገዙ ጊዜን ከመቆጠብ ባለፈ እንግልትን አስቀርቶልኛል" ብለዋል።

የሲዳማ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተርና የደንበኞች አገልግሎት የታክስ አወሳሰንና የገቢ አሰባሰብ ዘርፍ ሃላፊ ወይዘሮ ሙላት ዮሴፍ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በክልሉ ከ35ሺህ 816 በላይ የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህ ግብር ከፋዮችም በሰባት ተከታታይ ቀናት ውስጥ ከ220 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደተግባር ተገብቷል ብለዋል። 


 

በክልሉ ከሚገኙ 45 መዋቅሮች በ31ዱ የገቢ አሰባሰብ ሂደቱ በቴሌብር ታግዞ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፣ ዘመናዊ የግብር አሰባሰብ ሥርአት መዘርጋቱ ለግብር ከፋዮች ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ከማስቻሉ ባለፈ ህገወጥ ተግባራትን ለመከላከል እያገዘ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመዘርጋት ግብር ከፋዮች ንግድ ፈቃዳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሌሎች ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን የሚያገኙበት አሰራር መዘርጋቱ እንግልት ያስቀረ፣ ጊዜና ጉልበት የቆጠበ ነው ሲሉም ምክትል ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም