የክረምቱ ዝናብ የሚፈጥረውን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም እና ስጋቶችን ለመቀልበስ በትኩረት መስራት ይገባል-ኢንስቲትዩቱ - ኢዜአ አማርኛ
የክረምቱ ዝናብ የሚፈጥረውን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም እና ስጋቶችን ለመቀልበስ በትኩረት መስራት ይገባል-ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 7/2017 (ኢዜአ)፦የክረምቱ ዝናብ የሚፈጥረውን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም እና ስጋቶችን ለመቀልበስ በትኩረት መስራት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በሚቀጥሉት አስር ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ዝናቡ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የደቡብ ምዕራብ፣ምዕራብና ሰሜን ምዕራብ የሀገራችን አካባቢዎች ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ዝናብ እንደሚኖር አመላክቷል።
በምስራቅ፣ሰሜን ምስራቅ እና መካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ የዝናብ መጠንና ሥርጭት እንደሚኖርም እንዲሁ።
በሌላ በኩል በሰሜን ምስራቅ፤ መካከለኛው እና ምዕራብ የሀገራችን አካባቢዎች ላይ አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩ የአየር ሁኔታ ክስተቶች በመነሳት ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር ጠቁሟል።
የሚኖረው የዝናብ መጠን ለወቅቱ የግብርና ስራ እንቅሥቃሴ በአመዛኙ አዎንታዊ ሚና እንዳለው በማንሳት፤ የሚኖሩትን መልካም አጋጣሚዎች ለመጠቀም እና ስጋቶችን ለመቀነስ መስራት እንደሚገባም ገልጿል።
በሚኖረው የአየር ሁኔታ በአብዛኛው ተፋሰሶች ላይ ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው የገፀ ምድር የውሃ ፍሰት እንደሚኖር ኢንስቲትዩቱ በትንበያው ጠቅሷል።
አልፎ አልፎ ከሚኖር ከባድ ዝናብ ጋር ተያይዞ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ ተፋሰሶች፣ የከተማም ሆነ የገጠር አካባቢዎች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ፣ የወንዞች ከፍታ መጨመር ሊያስከትል እንደሚችልም አስጠንቅቋል።
በመሆኑም የሚመለከታቸው የዘርፉ አካላት ሊኖር የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችን ማዘጋጀትና የማፅዳት ስራ መስራት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥቷል።