ከተማ አስተዳደሩ የኩላሊት እጥበት ህክምና ተደራሽነትን ለማስፋት ከግሉ ዘርፍ ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ከተማ አስተዳደሩ የኩላሊት እጥበት ህክምና ተደራሽነትን ለማስፋት ከግሉ ዘርፍ ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 7/2017 (ኢዜአ)፦ከተማ አስተዳደሩ የኩላሊት እጥበት ህክምና ተደራሽነትን ለማስፋት ከግሉ ዘርፍ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለኩላሊት እጥበት ህክምና አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶችን ለዳግማዊ ምኒልክ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ድጋፍ አድርጓል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ከተማ አስተዳደሩ በሰው ተኮር ሥራዎቹ የኩላሊት እጥበት ህክምናን ለማስፋት እየሰራ ነው።
ከተማ አስተዳደሩ በዘውዲቱ እና በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታሎች የኩላሊት እጥበት ህክምና ወጪን በመሸፈን ታካሚዎች አገልግሎቱን በነጻ እንዲያገኙ ሲያደርግ መቆየቱን አውስተዋል።
በዚህም ከመላ ሀገሪቱ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ታካሚዎችን እንግልት ለመቀነስ መስራቱን ጠቅሰው፥ አገልግሎቱን ለማስፋትም ዳያስፖራውን ጨምሮ በመንግሥትና በግል አጋርነት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ይህም በመክፈል አቅም ማነስ ምክንያት የኩላሊት እጥበት ለማድረግ የሚቸገሩ ዜጎች ህክምናውን እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅሰዋል።
ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር ከተማ አስተዳደሩ የህክምናውን ተደራሽነት ለማስፋት አሁንም ከግሉ ዘርፍ ጋር ያለውን ትብብር ማጠናከሩንም ገልጸዋል።
ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ያደረገው የኩላሊት ህክምና ማሽንና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍም የትብብር ስራው ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የዛሬው ድጋፍ ታካሚዎቹ በሳምንት ሶስት ቀን የተሟላ የእጥበት ህክምና የሚያገኙበትን የማሽን እና የአልጋ ቁሳቁስ ያሟላ ነው ብለዋል ከንቲባዋ።
ድርጅቱ ህይወት በሚያድኑ ተግባራት እያደረገ ላለው ድጋፍም በማመስገን፥ በቀጣይም አቅም የሌላቸውን ዜጎች እና ህሙማንን የመደገፍ የጋራ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሃንስ ጫላ በበኩላቸው፥ ከዚህ ቀደም በዘውዲቱ መታሰቢያ እና በዳግማዊ ምኒልክ አጠቃላይ ስፔላይዝድ ሆስፒታሎች በ20 የኩላሊት እጥበት ማሽኖች ለ144 ታካሚዎች አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበር አውስተዋል።
የግብዓት ጉዳይ ፈታኝ ሆኖ መቆየቱን ያነሱት ኃላፊው፥ ዛሬ ከሜድሮክ የተረከቧቸው 20 የኩላሊት እጥበት ማሽን፣ 10 ዘመናዊ የታካሚዎች አልጋ እና ሌሎች የህክምና ግብዓቶች ፋይዳቸው የጎላ ነው ብለዋል።
የዛሬው ድጋፍ የታካሚዎችን ቁጥር በእጥፍ የሚያሳድግ እና ለቀጣይ ሶስት ዓመታት ያልተቋረጠ የኩላሊት እጥበት ህክምናን መስጠት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም በመዲናዋ የኩላሊት እጥበት ህክምና አገልግሎትን ለማስፋት ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ጠቁመዋል።
የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ፥ ሜድሮክ ለአቅመ ደካሞች እያደረገ እና የህሙማንን ህይወትን የሚታደግ ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸው፥ በዚህም ተቋማዊ ክብር እና ደስታ ይሰማናል ብለዋል።
ድርጅቱ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።