በክልሉ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል እና የተማሪዎች ምገባ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል

ባሕርዳር፤ ሐምሌ 7/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ  የመምህራን አቅም ግንባታ ፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ  የማሻሻል እና የተማሪዎች ምገባ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል  የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ። 

ቢሮው የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የቀጣይ አምስት አመት ስትራቴጅክ ዕቅድ  ትውውቅ መድረክ እያካሄደ ነው።


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል ማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤ ያለፈው የትምህርት ዘመን  ክፍተቶችን  በቀጣዩ ዘመን ለማካካስ የሚያስችል ዕቅድ ተይዞ  ከወዲሁ እየተሰራ ነው። 

የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ  አዲሱን የትምህርት ስርዓት ታሳቢ ያደረገ የመምህራን አቅም ግንባታ ፣የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል እና የተማሪዎች ምገባ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። 

በአዲሱ በጀት ዓመት  ከዚህ  ቀደም ያቋረጡትንና ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናትን በመመዝገብ ያለፉትን ዓመታት ሊያካክስ የሚችል ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

ስለትምህርት የማያገባው የሕብረተሰብ ክፍል እንደሌለ ያመለከቱት ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር) ፤  ለዕቅዱ መሳካት ሁሉም አካል ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

 በ2018 የትምህርት ዘመን  ከሰባት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ታቅዶ ከወዲሁ ዝግጀት እየተደረገ መሆኑም  ተመልክቷል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ የቢሮው አመራሮችና ሰራተኞች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም