በዞኑ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ምርትና አገልግሎታቸውን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ምርትና አገልግሎታቸውን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው

ነገሌ ቦረና፤ ሐምሌ 7/2017(ኢዜአ)፡- በምስራቅ ቦረና ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የስራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ምርትና አገልግሎታቸውን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ ተገለጸ።
በዞኑ የስራ እድል ፈጠና ክህሎት ጽህፈት ቤት የስራ እድል ፈጠራ ቡድን መሪ አቶ ጎዳና ሳራ፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በዞኑ ለ42ሺህ ወጣቶች የስራ እድል መመቻቸቱን ለኢዜአ ተናግረዋል።
ከእነዚህም መካከል ከ10ሺህ 560 በላይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ሰልጥነው የተመረቁ ናቸው ብለዋል፡፡
ነገሌ ቦረና ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ አጠቃላይ በዞኑ ወደ ስራ ከገቡት ወጣቶች መካከል 15ሺህ 971 ሴቶች እንደሆኑም አንስተዋል፡፡
ወጣቶቹ ወደ ስራ የገቡት በግብርና፣ በአገልግሎትና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ሲሆን፤ ግንባታ፣ ንግድ፣ እንስሳት እርባታ፣ ማዕድን ፍለጋና ግብይት፤ የቤትና የቢሮ እቃዎች ማመርተ ሰፊውን ድርሻ ይወስዳሉ ብለዋል።
ወደ ስራ ለገቡት ወጣቶች 78 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ብድር በማመቻቸት ትራክተር፣ ከ10 ሄክታር በላይ የማምረቻ እና መሸጫ ቦታና 61 የመሸጫ ሱቆች ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
ወደ ስራ የገቡ ወጣቶችም ምርትና አገልግሎታቸውን በብዛትና በጥራት ለገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪ አልዬ ዋቆ ከ3 ባልደረቦቹ ጋር በልብስ ስፌትና የአልባሳት ምርት አቅርቦት ስራ ከተሰማሩ ወጣቶች መካከል አንዱ ሲሆን፤ አልባሳቱ ባህልን ከማስተዋወቅ ባለፈ በገበያ አዋጭ በመሆኑ የተሻለ ገቢ የሚያስገኝ ተመራጭ የስራ ዘርፍ መሆኑን ገልጿል፡፡
በውጤቱም እራሳችንንና ቤተሰቦቻችንን ከመርዳት አልፈን ከንግድ ስራው የምናገኘውን ትርፍ መቆጠብ ጀምረናል ሲልም ተናግሯል፡፡
ሌላው የከተማው ነዋሪ ወጣት ቢኒያም አምሳሉና 2 ባልደረቦቹ በብረታ ብረት የስራ ዘርፍ የተሰማሩ ናቸው።
ወጣት ቢኒያም በሰጠው አስተያየት፤ ምርታችንን በጥራት እያመረትን ለነገሌ ቦረና ከተማ ህዝብና ለሴክተር መስሪያ ቤቶች ጭምር እያቀረብን ነው ብሏል።
አሁን ላይ ካፒታላቸው 150ሺህ ብር መድረሱን ገልጸው በቀጣይም ስራቸውን ለማስፋፋት ተጨማሪ ብድር ለመውሰድ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።