የምግብ ዋስትና እና የምግብ ሉዓላዊነት ልዩነት አላቸው? - ኢዜአ አማርኛ
የምግብ ዋስትና እና የምግብ ሉዓላዊነት ልዩነት አላቸው?

የምግብ ዋስትና እና የምግብ ሉዓላዊነት እሳቤዎች በዋናነት የሰው ልጆችን ምግብ የማግኘት መብት የሚያንጸባርቁ ናቸው።
ይሁንና የሁለቱ ጽንሰ ሀሳቦች ፍልስፍናቸው፣ አካሄዳቸውና ትግበራቸው ለየቅል ነው።
የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት(ፋኦ) የምግብ ዋስትና ማለት “ለሁሉም ሰው ሁልጊዜ በቂ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ፣ የምግብ ፍላጎትና ምርጫዎቹን እንዲያሟላ ንቁና ጤናማ ህይወት እንዲኖር ማድረግ ነው” ሲል ይገልጸዋል።
አቅርቦት፣ ተደራሽነት፣ መጠቀምና ደህንነት የምግብ ዋስትና ቁልፍ ምሰሶዎች መሆናቸውም ይጠቀሳል።
የምግብ ዋስትና አብዛኛው ውጤቶች የሚለኩት ረሃብን መከላከል እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን በመቅረፍ ነው።
አካሄዱም በመንግስታት ተጽእኖ ስር የወደቀ፣ በገበያ ምርት የሚመራና ዓለም አቀፋዊነቱ ጎልቶ የሚታይ መሆኑም እንዲሁ።
የምግብ ሉዓላዊነት እሳቤ የተጠነሰሰው እ.አ.አ በ1993 በቤልጂየም የተቋቋመው “LaVia Campesina” (የጢሰኞች መንገድ) የተሰኘው ዓለም አቀፍ የአርሶ አደሮች ድርጅት ነው።
ድርጅቱ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ መሬት የሌላቸው ሰራተኞች፣ አርሶ አደሮች (በተለይም አነስተኛ እና መካከለኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች)፣ አርብቶ አደሮች፣ የግብርና ሰራተኞች፣ ነባር ዜጎች፣ ሴት አርሶ አደሮች እና ስደተኞችን አቅፎ የያዘ ነው።
የዓለም አቀፍ ንቅናቄው ዋነኛ ጭብጥ ዜጎች የምግብ ስርዓታቸውን ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ራሳቸው በባለቤትነት መምራት እና ማስተዳደር አለባቸው የሚል ነው።
የምግብ ሉዓላዊነት ቁልፍ ጽንሰ ሀሳቦች ሀገር በቀል ቁጥጥር፣ ዘላቂ ስነ-ምህዳር መገንባትና የአርሶ አደሩን መብት ማስጠበቅ ነው።
ዋነኛ ትኩረቱ በምግብ ምርት እና ስርጭት ላይ ራስ ገዝ መሆንና በራስ አቅም መወሰን እንደሆነ መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን አካሄዱ መብት እና ማህበረሰብን ያማከለ እንዲሁም ባለቤትነትን መጠበቅ መሰረት ያደረገ ነው።
የምግብ ዋስትና የሚበላ በቂ ምግብ አለ ወይ? በሚል ጥያቄ ውስጥ የሚጠቀለል እሳቤ ሲሆን የምግብ ሉዓላዊነት ሰዎች ምን እንደሚበሉ እና እንዴት እንደሚበሉ መቆጣጠር ይችላሉ ወይ? የሚለው ጉዳይ ላይ ያተኩራል።
የምግብ ዋስትና በምግብ የማግኘት መብት ውስጥ የመጀመሪያ ወሳኝ መንደርደሪያ ቢሆንም ያለ ምግብ ሉዓላዊነት ምሉዕ ውጤት ማግኘት እንደማይቻል የተለያዩ ጽሁፎች ያመለክታሉ።
የምግብ ዋስትና የምግብ ተደራሽነትን ሊያሻሽል ቢችልም በምግብ ስርዓት ውስጥ ላሉ መዋቅራዊ ኢ-ፍትሃዊነቶች እና ዘላቂ ያልሆኑ አካሄዶች ምላሽ መስጠት አይችልም።
የምግብ ሉዓላዊነት በቀጥታ መዋቅራዊ ጉዳዮችን ይነካል። ሀገራት የምግብ ምርት እና ስርጭትን ጨምሮ አጠቃላይ የምግብ ስርዓትን ሀገራት በራሳቸው እንዲቆጣጠሩ የሚሟገት እሳቤ እና መንገድ ነው።
የስነ ምግብ ባለሙያዎች የምግብ ሉዓላዊነት የሚያረጋግጥ ሀገር በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ የምግብ ዋስትና የማረጋገጥን ጥያቄ እንደሚመልስ ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያም በምግብ ስርዓት ሽግግር ከምርት እስከ ተጠቃሚ ባለው ሰንሰለት በራሷ በመቆጣጠር የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ እየሰራች ትገኛለች።
የዜጎችን የምግብ ፍላጎት በራስ የምርት አቅም የመሙላት ስራ በማከወን ከውጭ ሀገራት ምርት ጠባቂነት ለመላቀቅ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ውጤት እያስገኙ ነው።
ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ከልመና ወጥታ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ውጭ ገበያ መላክ መጀመሯ ታሪካዊ ድል ሲሆን ከውጭ የኢኮኖሚ ጥገኝነት በመላቀቅ የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነት ለማስከበር በስንዴ ልማት የተመዘገበውን ስኬት በሌሎች የግብርና መስኮች ለመድገም በመሰራት ላይ ይገኛል።
በሩዝ፣ አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ ሻይ ቅጠልና ሌሎች የተለያዩ ሰብሎች ላይ እየተከናወነ ያለው ስራ ተጨባጭ ውጤቶች እያስገኘ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በምግብ ዋስትናና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላሳዩት ርዕይ፣ የአመራር ቁርጠኝነት ከዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት(ፋኦ) የአግሪኮላ ሜዳልያ በጥር ወር 2016 ዓ.ም ያበረከተው ሽልማት ለምግብ ሉዓላዊነት ጥረት የተሰጠ እውቅና ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የኢትዮጵያ መንግስት ረሃብን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት እና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በዚህም ብሔራዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ እየሰራ መሆኑን በሽልማቱ ወቅት ገልጸው ነበር።
ኢትዮጵያ በርካታ ያልተነኩ ጥሬ ሃብቶች፣ ተስማሚ የአየር ንብረትና ለስራ ትጉ የሆነ ወጣት እንዳላትና እነዚህን ሃብቶች ታሳቢ በማድረግ ሀገሪቱን በልማት ወደ ፊት ማራመድ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ዋጋ እንደከፈልን ሁሉ ከምግብ ጥገኝነት ለመላቀቅ በትጋት መስራት እንደሚገባ ተናግረው ነበር።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነት ማግኘት አለባት፤ አምርታ መብላት ያልቻለች ሀገር ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማረጋገጥ ትቸገራለች በሚል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ግብ ይዘን ሰርተናል ብለዋል።
በዚህ እሳቤ 23 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ከሴፍቲኔት ተረጂነት ነጻ መውጣታቸውን ጠቁመው ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ የምግብ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች ሀገር ማድረግ አለብን ለዚህም ሰፊ የሚታረስ መሬት እለን ማለታቸው ይታወሳል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በተመሳሳይ ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ያስመዘገበችውን አኩሪ ድል በዘመናዊ ግብርና የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ እንደግመዋለን ሲሉ ገልጸው ነበር።
የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ሀገራዊ ትልም ኢትዮጵያን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በማሸጋገር ለተሟላ ሀገራዊ ክብር፣ ነጻነት እና ሉዓላዊነት የሚያሸጋግር መልካም ጅማሮ ነው።
ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ በኢትዮጵያ እና በጣልያን በጋራ አዘጋጅነት ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ በስርዓት ምግብ ትራንስፎርሜሽን፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና በግብርናው ዘርፍ ባደረጋቻቸው ሀገር በቀል ሪፎርሞች ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች ጉባኤውን እንድታስተናግድ ለመመረጥ ምክንያቶች ናቸው።
ኢትዮጵያ በስርዓተ ምግብ ለውጥ ውስጥ እየተወጣች ያለው የመሪነት ሚና እና በማደግ ላይ ከሚገኙ ሀገራት በስርዓተ ምግብ ተምሳሌት የሆነች ሀገር መሆኗ ተመድ ዓለም አቀፉን ከፍተኛ ጉባኤ በኢትዮጵያ እንዲያደርግ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል።
በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያ የስርዓተ ምግብ ሽግግርን ለማሳካት እያከናወነች ባለው ተግባር ዙሪያ ተሞክሮዋን ለዓለም ማህበረሰብ የማሳወቅ ስራ ታከናውናለች።