በሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ሩብ ፍጻሜውን የሚቀላቀሉ ቀሪ ሀገራት የሚለዩባቸው ጨዋታዎች ይደረጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ሩብ ፍጻሜውን የሚቀላቀሉ ቀሪ ሀገራት የሚለዩባቸው ጨዋታዎች ይደረጋሉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 7/2017(ኢዜአ)፦ በ13ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ሶስት የመጨረሻ መርሃ ግብር ዛሬ ይካሄዳል።
ከምሽቱ 4 ሰዓት ደቡብ አፍሪካ ከማሊ በሆነር ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ደቡብ አፍሪካ እና ማሊ በተመሳሳይ አራት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል።
የጨዋታው አሸናፊ የምድቡ መሪ በመሆን ሩብ ፍጻሜ መግባቱን ያረጋግጣል።
አቻ መውጣት በሂሳባዊ ሁለቱን ቡድኖች ሩብ ፍጻሜውን እንዲቀላቀሉ የሚያስችላቸው እድል አለ።
ሀገራቱ ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ በውድድር ጨዋታዎች ተገናኝተው ደቡብ አፍሪካ ሁለቱንም ጨዋታዎች አሸንፋለች።
ደቡብ አፍሪካ በጨዋታዎቹ ስድስት ግቦችን ስታስቆጥር ማሊ ምንም ግብ ከመረብ ላይ አላሳረፈችም።
እ.አ.አ በ2010 በደቡብ አፍሪካ አስተጋጅነት በተካሄደው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ተገናኝተው አዘጋጇ ሀገር ማሊን 4 ለ 0 አሸንፋለች።
ቁጥራዊ መረጃዎች የደቡብ አፍሪካን የበላይነት ቢያሳዩም በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የምትገኘው ማሊ በዛሬው ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር እንደምታደርግ ይጠበቃል።
በምድብ ሶስት ጋና ከታንዛንያ በተመሳሳይ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ በቤርካኔ ሙኒሲፓል ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ታንዛንያ እና ጋና በተመሳሳይ አንድ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሶስተኛና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ሁለቱ ቡድኖች ወደ ሩብ ፍጻሜ ለመግባት ሶስት ነጥብ ማግኘት ግድ ይላቸዋል። ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን የደቡብ አፍሪካ እና የማሊን ጨዋታ ውጤት ይጠብቃሉ።
የጨዋታው አሸናፊ በሂሳባዊ ስሌት ምርጥ ሶስተኛ ወይም በቀጥታ ወደ ሩብ ፍጻሜ የመግባት እድል አለው።
በሶስት ምድብ ተከፍሎ በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው 13ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ከየምድቡ አንደኛ እና ሁለተኛ የሚወጡ ሀገራት ለሩብ ፍጻሜ ያልፋሉ።
ከምድቦቹ ምርጥ ሶስተኛ ሆነው የሚያጠናቅቁ ተጨማሪ ሁለት ሀገራት ሩብ ፍጻሜውን ይቀላቀላሉ።