የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በሪፎርም ስራዎቹ ኢትዮጵያን የሚመጥን ዘመናዊ አሰራር ገንብቷል - ኢዜአ አማርኛ
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በሪፎርም ስራዎቹ ኢትዮጵያን የሚመጥን ዘመናዊ አሰራር ገንብቷል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 7/2017(ኢዜአ)፦ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ባከናወናቸው የሪፎርም ስራዎች ኢትዮጵያን የሚመጥን ዘመናዊ አሰራር መገንባቱን የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ገለጹ።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከክልል መዝጋቢ እና ባለድርሻ አካላት ጋር የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ያተኮረ ጉባኤ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት፣ የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሀሰን፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራር እና አባላት እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ታድመዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ ሰላማዊት ዳዊት በመክፈቻ ንግግራቸው፥ አገልግሎቱ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በርካታ ችግሮች እንደነበሩበት አስታውሰዋል።
ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ከማሟላት አንጻርም ጉድለቶች እንደነበሩ በመጥቀስ፥ አገልግሎቶቹ ከማህበረሰቡ ፍላጎት ጋር ያልተጣጣሙ ሆነው መቆየታቸውን አንስተዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ፈጣንና ሁሉን አቀፍ ሪፎርም በማድረግ የብልጽግና ጉዞ ላይ እንደምትገኝ ጠቅሰው አገልግሎቱም ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሪፎርም ማካሄዱን ገልጸዋል።
ለዚህም 11 የሪፎርም አጀንዳዎች ተቀርጸው ወደ ስራ መገባቱን በማውሳት፥ ኋላቀር የነበረውን የባዮሜትሪክ መረጃ መቀበያ ስርዓት ወደ ዘመናዊ አሰራር መቀየር መቻሉን ተናግረዋል።
በዚህም የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት በማተም ችግሩን በጉልህ መቅረፍ መቻሉን ተናግረው ከአስር በላይ የጉዞ ሰነዶች እንዲዘምኑ መደረጋቸውን አስረድተዋል።
የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማዘመን ወደ ዲጂታላይዜሽን ስኬታማ ሽግግር መደረጉን ገልጸው፥ በተቋሙ የሪፎርም ሥራዎች ኢትዮጵያን የሚመጥን ዘመናዊ አሰራር ገንብተናል ነው ያሉት።
ከዜጎች ፍላጎት አንጻር በ2018 በጀት ዓመት አገልግሎቱን ይበልጥ በማዘመንና በማቀላጠፍ የህዝብ እርካታን ለማሳደግ ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል።
ባለድርሻ አካላትም ለአገልግሎቱ ግብ መሳካት ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።