ቼልሲ ፒኤስጂን ባልተጠበቀ ሁኔታ በማሸነፍ የዓለም ክለቦች ዋንጫን አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
ቼልሲ ፒኤስጂን ባልተጠበቀ ሁኔታ በማሸነፍ የዓለም ክለቦች ዋንጫን አሸነፈ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 6/2017 (ኢዜአ)፦ በፊፋ ክለቦች ዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ቼልሲ ፒኤስጂን 3 ለ 0 አሸንፏል።
ማምሻውን በሜትላይፍ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ኮል ፓልመር ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ጆአኦ ፔድሮ ቀሪዋን ጎል ለሰማያዊዎቹ ከመረብ ላይ አሳርፏል።
የፒኤስጂው ጆአኦ ኔቬስ በ86ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
በጨዋታው ፒኤስጂ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወስድም ቼልሲ ወደ ሜዳ ይዞ በገባው የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ውጤታማ ሆኗል።
ቼልሲ ኳስ በሚያዝበት አጋጣሚዎች ከተጋጣሚው የበለጠ አስፈሪ ነበር።
የፒኤስጂ የመሐል ክፍል ተጫዋቾች እንደ ልባቸው እንዳይጫወቱ የማድረግ እቅድ ይዞ የገባው ቼልሲ የተሳካላት ሲሆን የፓሪሱን ክለብ ፈጣን የክንፍ መስመር ተጫዋቾች እንቅስቃሴ መግታት ችሏል። ሰማያዊዎቹ በመከላከሉ ረገድም የተዋጣላቸው ነበሩ።
ቼልሲ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊውን በመርታት የዓለም ክለብ ዋንጫን አንስቷል።
በጨዋታው ሁለት ጎል ያገባው እና አንድ ለግብ ያቀበለው ኮል ፓልመር የጨዋታ ኮከብ ሆኖ ተመርጧል።
ውጤቱ የዓለም እግር ኳስ አፍቃሪ ያልተጠበቀው ነው። የፈረንሳዩ ቡድን ጨዋታውን ያሸንፋል የሚል ሰፊ የቅድሚያ ግምት አግኝቶ ነበር።
የምዕራብ ለንደኑ ክለብ በዩኤፋ ኔሽንስ ሊግ ጨዋታው የዓለም ዋንጫ ክብር ጨምሯል።
ፒኤስጂ በአስደናቂው የውድድር ዓመት ጉዞ አምስተኛው ዋንጫ የማንሳት ህልሙ አልተሳካም።
ቼልሲ ከዋንጫው በተጨማሪ የ40 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሽልማት አግኝቷል።
የቼልሲው ኮል ፓልመር የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች በመባል ተመርጧል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፍጻሜውን ጨዋታ በሜትላይፍ ስታዲየም ተገኝተው ተከታትለዋል።