በዞኑ የህብረት ስራ ማህበራትን አቅም በማጠናከር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የህብረት ስራ ማህበራትን አቅም በማጠናከር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው

ደብረማርቆስ ፤ ሐምሌ 6/2017(ኢዜአ)፦ በምስራቅ ጎጃም ዞን የህብረት ስራ ማህበራትን አቅም በማጠናከር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ።
የዞኑ ግብርና መምሪያ 17 የእርሻ ትራክተሮችና ኮምባይነሮችን ለሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራትና ባለሀብቶች ዛሬ አስረክቧል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኑርልኝ ብርሃኑ እንዳሉት በዞኑ የህብረት ስራ ማህበራትን አቅም በማጠናከር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው።
የምርታማነት ማደግ የአርሶ አደሩን የኑሮ ደረጃ ከማሻሻል ባለፈ ገበያን በማረጋጋት የዋጋ ንረትን በመቀነስ ረገድ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።
የዞኑን የምርታማነት አሁን ካለበት ለማሳደግ የሜካናይዜሽን ግብርናን ማስፋፋትና ተደራሽ ማድረግ የህልውና ጉዳይ ሊሆን ይገባል ያሉት ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ መኮንን ናቸው።
ለዚህም የክልሉ መንግስት ባደረገው ድጎማ ዘጠኝ ትራክተሮችና ስድስት ኮምባይነሮችን ለሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራት ድጋፍ ማድረግ እንደቻለም ተናግረዋል።
በተጨማሪም በረጅም ጊዜ ክፍያ ለሁለት ባለሀብቶች ሁለት ትራክተሮች ቀርበው ርክክብ መደረጉን ገልጸዋል።
የክልሉ ህብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ አማካሪ አቶ ሃይለ ልኡል ተስፋ በበኩላቸው የሜካናይዜሽን ግብርና ተደራሽነት እንዲሰፋ አልሚ ባለሃብቶችን ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ እና ብድር እንዲያገኙ የሚደረገው ጥረት እንዲጠናከር ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራት በራሳቸው አቅም የሜካናይዜሽን እርሻን እንዲያስፋፉ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግላቸውም ገልፀዋል።
በእነማይ ወረዳ የልምየት የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር አባል አርሶ አደር ብርቄ ጸጋዬ እንዳሉት ''የሜካናይዜሽን አቅርቦት ድጋፍ መደረጉ በስራችን እንድንበረታ የሚያደርግ ነው'' ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ሜካናይዜሽን ባለመኖሩ በባህላዊ አስተራረስና የምርት አሰባሰብ ጊዜያቸውን ያባክኑ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ግን በአካባቢው የሜካናይዜሽን እርሻ መጀመሩ የአርሶ አደሩን ችግር ያቃልላል የሚል ተስፋ ማሳደሩንም አርሶ አደር ብርቄ ተናግረዋል።
በዞኑ ለምርት ዘመኑ ከ642 ሺህ ሄክታር በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በዚህም ከ25 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚገኝም ተገልጿል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን በሰብል ከሚሸፈነው መሬት 58 በመቶ የሚሆነው በትራክተር ለመታረስ ምቹ መሆኑም ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።