የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ ያደረጋቸው የኢኮኖሚ ሪፎርሞች የህንድ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ያላቸው ተሳትፎ እንዲጨምር ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ ያደረጋቸው የኢኮኖሚ ሪፎርሞች የህንድ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ያላቸው ተሳትፎ እንዲጨምር ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 6/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ ያደረጋቸው የኢኮኖሚ ሪፎርሞች የህንድ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ያላቸው ተሳትፎ እንዲጨምር ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ ናቸው ሲሉ በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ ገለጹ።
የኢኮኖሚ ሪፎርሙ መንግሥት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑንም አምባሳደሩ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ተግባራዊ የተደረጉ የኢኮኖሚ ሪፎርሞች በህንድ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ናቸው።
መንግስት ከወሰዳቸው የሪፎርም እርምጃዎች መካከል የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያው እንዲወሰን መደረጉ፣ የውጭ አገር ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት መሆን የሚችሉበት አዋጅ መጽደቁ የውጭ ባለኃብቶችን ተሳትፎ የሚያሳድግ ትልቅ እርምጃዎች ናቸው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ለውጭ ባለኃብቶች ዝግ የነበሩ የኢኮኖሚ መስኮች ክፍት መደረጋቸው የውጭ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ መፈቀዱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የህንድ ኩባንያዎችም በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቁመው፤ በማዕድን፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በባንክና ፋይናንስ፣ የካፒታል ገበያ በርካታ ቁጥር ያላቸው የህንድ ባለኃብቶች ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመዋል።
በግብርናው መስክም ኢትዮጵያ ውጤታማ ለመሆን የሚያስችሉ እምቅ አቅም እንዳላት የገለጹት አምባሳደሩ፤ ሰፊ የሚታረስ መሬት፣ የውኃ ኃብት የሰው ኃይልና ሌሎች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የሚስቡ አቅሞች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የህንድ ባለኃብቶችም በግብርናው ዘርፍ በሰብል ልማት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በአበባ ልማት እንዲሁም ለመድሃኒት ምርት ግብዓት የሚውሉ ተክሎች ልማት ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸውም አንስተዋል።
በንግድና በኢንቨስትመንት በኩልም በአገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ በዚህም ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ለማሳለጥ የሚረዳ የጋራ የንግድ ኮሚሽን መቋቋሙን ገልጸው፤ ኮሚሽኑ ግንኙነቱን በሚያሳድጉ ጉዳዮች ላይ እየተወያየ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ በየዘርፉ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ገለጻ እያገኘን ነው ያሉት አምባሳደሩ በአገራቱ መካከል ያለው ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን አብራርተዋል።
የብሪክስ የትብብር ማዕቀፍም አገራቱ ግንኙነታቸውን ይበልጥ እንዲያሳድጉ ዕድል መፍጠሩን አስረድተዋል።