በመዲናዋ በከተማ ግብርና ከ159 ሺህ በላይ አዳዲስ ተጠቃሚዎች ወደ ስራ ገብተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ በከተማ ግብርና ከ159 ሺህ በላይ አዳዲስ ተጠቃሚዎች ወደ ስራ ገብተዋል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 6/2017(ኢዜአ)፦በ2017 በጀት ዓመት ከ159 ሺህ በላይ አዳዲስ ተጠቃሚዎች ወደከተማ ግብርና ስራ መግባታቸውን የአዲስ አበባ የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ገለጸ።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር መሰለ አንሸቦ ለኢዜአ እንደገለጹት የከተማ ግብርና በተለይ የሌማት ትሩፋት መርኃ ግብር ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጤታማነቱ እየጨመረ መጥቷል።
ኮሚሽኑ በበጀት አመቱ በዘርፉ ለተሰማሩ ነዋሪዎች አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረጉን ገልፀው፤ ቀደም ብለው ወደ ዘርፉ የገቡትን አጠናክሮ የማስቀጠልና አዳዲስ ስራ ጀማሪዎችን ወደ ስራ የማስገባት ስራ በትኩረት መስራቱን አንስተዋል።
በኅብረተሰቡ ዘንድ በትንሽ ሥፍራ የከተማ ግብርናን ተግባራዊ በማድረግ ከራስ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ትርፋማ መሆን እንደሚቻል የግንዛቤ ፈጠራ ስራ በስፋት መሰራቱንም ተናግረዋል።
በዚህም ካሁን ቀደም በዘርፉ የተሰማሩትን ከማስቀጠል ባለፈ በበጀት ዓመቱ 159 ሺህ 686 አዳዲስ ዜጎችን ወደ ዘርፉ ማስገባት መቻሉን ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል በመዲናዋ የሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ 2 ሺህ 565 ተቋማት ወደ ግብርና ስራ እንዲገቡ መደረጉን ጠቁመዋል።
ከነዚህም መካከል 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎች እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደሚገኙበት ጠቅሰው፤ ሰራተኞች ምርቶችን በተመጣጣኛ ዋጋ ገዝተው እንዲጠቀሙ እድል መፍጠሩንም ገልጸዋል።
የከተማ ግብርና ልማት በገበያ የምርት እጥረት እንዳይኖር ከማድረግ ባሻገር በበጀት አመቱ ለ9 ሺህ 526 ወጣቶች የስራ እድል መፍጠሩን ጨምረው ገልፀዋል።
በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር፣ በእንስሳት እርባታ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ላይ በመሰማራት ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የመዲናዋ ነዋሪዎች የተናገሩት።
በዘርፉ ከተሰማሩት መካከል ወጣት ነብዩ ማሞ በግል ተቋም ተቀጥሮ ይሰራ እንደነበረ ገለፆ፤ የከብት እርባታ ስራ ከጀመረ ወዲህ ግን ትርፋማ መሆኑን ተናግሯል።
በዚህም በውስን በጎችና በአንድ ላም የጀመረው ስራ አሁን ላይ የተሻለ ውጤት እያስገኘለትና ከራሱ አልፎ ለሌሎች ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር እንዳስቻለው ጠቅሷል።
በወተት ላም እርባታ፣ በዶሮ እርባታና እንቁላል ምርት ላይ በመሰማራት ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚገልጹት ደግሞ አቶ ፋሲል አዘነ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው።
አቶ ፋሲል ከ3 አመት በፊት ስራውን ሲጀምሩ ከ6 ላሞች በቀን 125 ሊትር ወተት ለገበያ ሲያቀርቡ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ወደ 57 ላሞች በማርባት በቀን 250 ሊትር ወተት ለገበያ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር መቻላቸውንም ነው የተናገሩት ።