''አካባቢን ፅዱ ለማድረግ በሚሰበሰብ ቆሻሻ ህይወት እንደሚለወጥ ማሳያው እኔ ነኝ''

ሀዋሳ ፤ ሐምሌ 6/2017(ኢዜአ)፦ ከየአካባቢው የሚወጣውን ቆሻሻ በአግባቡ በመሰብሰብ ከራስ አልፎ ለሌሎች የስራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻል የሀዋሳ ከተማ ነዋሪው አቶ ሄኖክ ዶንጋቶ ራሳቸውን በዋቢነት ይጠቅሳሉ፡፡

አቶ ሄኖክ ዶንጋቶ በሀዋሳ ከተማ ቆሻሻ በመሰብሰብ ህይወታቸውን ቀይረው ለሌሎች የስራ ዕድል ያመቻቹ ግለሰብ ናቸው። 


 


 

አቶ ሄኖክ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባል የነበሩና በግዳጅ ላይ በደረሰባቸው ጉዳት ያለስራ ቆይተው ኋላ ላይ በሀዋሳ ከተማ ቆሻሻን ወደ መሰብሰብ ስራ መግባታቸውን ይናገራሉ።

ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ከየቤቱና ተቋማቱ የሚወጣውን ቆሻሻን የእጅ ጋሪን በመጠቀም በከተማው ከሌሊቱ 9 ሰዓት ጀምሮ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “ ቆሻሻ ያለው!!! ቆሻሻ ያለው” በማለት የመሰብሰብ ስራ የየዕለት ተግባራቸው መሆኑን ይገልፃሉ።

አሁን ላይ ከሀዋሳ ከተማ ከሚሰበሰበው አጠቃላይ የቆሻሻ መጠን 35 በመቶ የሚሆነውን እየሰበሰቡ መሆኑን ያስረዱት አቶ ሄኖክ ከየሰፈሩ በሚወጣው ቆሻሻ ጥቅም ማግኘት ብቻም ሳይሆን አካባቢው ፀድቶ ሲመለከቱት ከፍተኛ እርካታ እንደሚሰማቸው ይናገራሉ።


 

በቆሻሻ መሰብሰብ ስራው ላይ በመሰማራታቸው ከወዳጆቻቸው ከፍተኛ ትችት ቢገጥማቸውም "የሚጠቅመኝን የማውቀው እኔ ነኝ፤ በማለት በትጋት በመስራት ከራሴ አልፌ ለሌሎች የስራ ዕድልን መፍጠር ችያለሁ'' በማለት ምላሽ ይሰጣሉ።፡

በ2010 ዓ.ም ሌሎች 12 የቤተሰብ አባላትን በመያዝ ህጋዊ ዕውቅና ያለው ማህበር መመስረታቸውን ያወሱት አቶ ሄኖክ "ቆሻሻን ወደ ሀብትነት በመቀየር ከራሳችን አልፈን ለበርካቶች የስራ ዕድል ፈጥረናል" ሲሉም ያክላሉ፡፡

ማህበሩ ከ134 በላይ ለሚሆኑ ሰራተኞች ቋሚ የስራ ዕድል መፍጠሩን ገልፀው ቆሻሻን ከተለያዩ አካባቢዎች በማሰባሰብ ወደ ማህበሩ የሚያቀርቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የገቢ ምንጭ መሆን መቻሉንም አውስተዋል፡፡

ከከተማው ከሚሰበሰበው ቆሻሻ የማይበሰብሰውን የፕላስቲክ ምርት በመጭመቅ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል ወደ አዲስ አበባ ከመላክ ባሻገር በተፈጥሮ ማዳበሪያ ሽያጭ ማህበሩ ወደ 300 ሺህ ብር የሚጠጋ ገቢ ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡

የአቶ ሄኖክ ባለቤት ወይዘሮ መሰረት ድጋሎ ''ቆሻሻን ብዙዎች የሚጸየፉት ቢሆንም ለእኛ ግን ህይወታችንን የቀየርንበትና ለብዙዎች የስራ ዕድል የፈጠርንበት የገቢ ምንጫችን ነው'' ብለዋል፡፡


 

ማህበሩ ቆሻሻ በአግባቡ ከተያዘ ሀብት መሆኑን በተጨባጭ እያሳየ ነው ያሉት ደግሞ የማህበሩ ኃላፊ አቶ አልታዬ ቦቦላ ናቸው።

ማህበሩ ከቆሻሻ ገቢ ከማግኘት ባለፈ ሀገራዊ የጽዳት ስራ ላይ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል፡፡


 

ከሌሊቱ 9 ሰዓት ጀምሮ በሀዋሳ ከተማና ሌሎች ወኪሎች ባሉባቸው ከተሞች ከግለሰቦች መኖሪያ ቤት፣ ከሆቴሎችና ከተለያዩ ድርጅቶችና ፋብሪካዎች ቆሻሻን በመሰብሰብና በመለየት የፕላስቲክ ቆሻሻ በተፈጥሮ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት እየተከላከሉ እንደሚገኙም ገልፀዋል።

ቆሻሻን ሰብስቦ ወደ ሀብትነት በመቀየር ሂደት ትልቁ ተግዳሮት "ቆሻሻን ለይቶ የማስቀመጥ ባህል ያለማደግ ነው" ያሉት አቶ አልታዬ በዚህ ላይ ግንዛቤን መፍጠር እኛን ጨምሮ ከሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ይጠበቃል ብለዋል።

በማህበሩ የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው መካከል አቶ አዲሱ ኩኬ ከመንግስት ስራ በጡረታ ከተገለሉበት ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ በዚህ ማህበር በመቀጠር ቤተሰባቸውን በኢኮኖሚ የሚደጉሙበት ዕድል እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡


 

በሲዳማ ክልል ደን አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የአከባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ቲቦ በክልሉ ከፕላስቲክ ብክለት የጸዳ አካባቢን ለመፍጠር በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ ነው ብለዋል::


 

ከቆሻሻ የጸዳ አካባቢ ለመፍጠር በሚደረግ ጥረት ከግንዛቤና ቆሻሻን ለይቶ ከመሰብሰብና መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ከማድረግ አንፃር ተግባሩ ተጠናክሮ እየተከናወነ መሆኑን ነው አቶ ዮሴፍ ያነሱት::

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም