የአውሮፓ ኃያላኑ ቼልሲ እና ፒኤስጂ የክለቦች ዓለም ዋንጫን ለማንሳት ይፋለማሉ - ኢዜአ አማርኛ
የአውሮፓ ኃያላኑ ቼልሲ እና ፒኤስጂ የክለቦች ዓለም ዋንጫን ለማንሳት ይፋለማሉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 6/2017(ኢዜአ)፦ በፊፋ ክለቦች የዓለም ዋንጫ ቼልሲ እና ፒኤስጂ ዛሬ የፍጻሜ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፍጻሜው ጨዋታ ላይ ይታደማሉ።
የፍጻሜው ጨዋታ 82 ሺህ 500 ተመልካች በሚያስተናግደው ሜት ላይፍ ስታዲየም ምሽት 4 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።
ቼልሲ በግማሽ ፍጻሜው የብራዚሉን ፍሉሜኔንሴን 2 ለ 0 አሸንፏል። ፒኤስጂ ሪያል ማድሪድ 4 ለ 0 በመርታት ለፍጻሜው አልፏል።
ቼልሲ እና ፒኤስጂ ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 10 የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ፒኤስጂ 5 ጊዜ ሲያሸንፍ ቼልሲ 2 ጊዜ አሸንፏል። 3 ጊዜ አቻ ወጥተዋል።
ሁለቱ ቡድኖች ስምንት ጊዜ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተገናኝተው ፒኤስጂ 3 ጊዜ ድል ሲቀናው ቼልሲ 2 ጊዜ አሸንፏል። በቀሪዎቹ ሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል።
አስደናቂው ፒኤስጂ የአሸናፊነት ስነ ልቦናው፣ የተከላከይ መስመሩ ጥንካሬ፣ የአማካይ ክፍሉ ኳስ የመቆጣጠር ብቃት እና ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴው ከብዙዎች አድናቆት እያስቸረው ነው።
የፓሪሱ ክለብ በክለቦች ዓለም ዋንጫ እስከ አሁን ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አምስት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። 16 ግቦችን ሲያስቆጥር ያስተናገደው አንድ ግብ ብቻ ነው።
ቡድኑ ከስድስቱ ጨዋታዎች በአምስቱ ግብ አልተቆጠረበትም።
የተከላካይ መስመር ክፍሉ ተጋላጭነት፣ የትኩረት ማጣት አጋጣሚዎች እና ግብ የመፍጠር ኃላፊነት በተወሰኑ ተጫዋቾች ላይ የተንጠለጠለ መሆኑ ፒኤስጂ እንደ ድክመት ሊነሱበት የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው።
ተጋጣሚው ቼልሲ በወጣቶች እና የመጫወት ረሃብ ባላቸው ባለክህሎቶች የተሞላ ነው።
የአማካይ ክፍሉ ጥንካሬ እና ሚዛን፣ የታክቲክ ተለዋዋጭነት እና የታክቲክ ተገዢነት እንዲሁም የማጥቃት አቅም የምዕራብ ለንደኑ ቡድን የጥንካሬ መገለጫዎች ናቸው።
ቡድኑ በውድድሩ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አምስት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏልክ። 14 ግቦችን ሲያስቆጥር 5 ግቦች ተቆጥረውበታል።
የተከላካይ ክፍሉ የአደጋ ተጋላጭነት፣ ልምድ ማነስ እና የጎል ማስቆጠር ያሉ ችግሮች አንድ ድክመት ይነሱበታል።
ፒኤስጂ ከፈረንሳይ ሊግ 1፣ የፈረንሳይ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ እና የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ድሉ በኋላ አራተኛውን ዋንጫ ለማንሳት ይፋለማል።
ቼልሲ ከአውሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ድሉ ላይ የክለቦች የዓለም ዋንጫን ለመጨመር ይጫወታል።
ፒኤስጂ ጨዋታውን የማሸነፍ ሰፊ ግምቱን ቢውሰድም ዋንጫ ካየ ወደ ኋላ ከማይለው ቼልሲ ጠንካራ ፈተና ይጠብቀዋል።
የኢራን እና አውስትራሊያ ጥምር ዜግነት ያላቸው የ47 ዓመቱ አሊሬዛ ፋግሃኒ ተጠባቂውን የፍጻሜ ጨዋታው በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፍጻሜውን ጨዋታ በሜትላይፍ ስታዲየም ተገኝተው እንደሚከታተሉ ተረጋግጧል።
የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ለውድድሩ ተሳታፊዎች በአጠቃይ የአንድ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሽልማት አዘጋጅቷል።
ውድድሩን የሚያሸንፈው ቡድን የ40 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሽልማት ያገኛል። ለፍጻሜ ያለፉ ቡድኖች ለፍጻሜ በማለፋቸው ብቻ 30 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ይበረከትላቸዋል።