ለፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ከ19 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ነዋሪዎች ተመዝግበዋል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 6/2017(ኢዜአ)፦ለፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ እስካሁን ከ19 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ነዋሪዎች መመዝገባቸውን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የህግና ፖሊሲ ዘርፍ ኃላፊ ጋብሬላ አብርሃም ገለጹ።

በኢትዮጵያ የነዋሪዎችን የመታወቅ መብት ለማረጋገጥ፣ በአገልግሎት ሰጭና ተቀባዮች መካከል መተማመን እንዲዳብር፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና የተሳለጠ አሰራር ለመዘርጋት  የዲጂታል መታወቂያ ገቢራዊ ተደርጓል፡፡

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የህግና ፖሊሲ ዘርፍ ኃላፊ ጋብሬላ አብርሃም ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት በአዲስ አበባ እና በክልል የዲጂታል የመታወቂያ ምዝገባ ማከናወንና ከተቋማት ጋር ትስስር መፍጠር በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ፡፡

ይህንን ተከትሎ እስካሁን  19 ነጥብ 1 ሚሊዮን ነዋሪዎች ለፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መመዝገባቸውንና  ከ55 ተቋማት ጋር ትስስር መፍጠር መቻሉን  ተናግረዋል ፡፡


 

በ2018 በጀት አመት የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባን የበለጠ ለማሳደግ እቅድ መያዙንና ከተቋማት ጋር ያለውን ትስስር ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡ 

በተለይ በክልሎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባን ይበልጥ ለማስፋት ከተቋማት ጋር ያለውን ትስስር ለማጠናከር ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት አመት በክልሎች የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባን በተመለከተ ሰፊ የግንዛቤ ስራ መሰራቱን እና በዚህም ውጤት መገኘቱንም አስታውቀዋል።


 

ለዚህ ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ ለስራው ትኩረት ሰጥቶ ህብረተሰቡ የዲጂታል መታወቂያ እንዲመዘገብ በማድረግ በኩል ትልቅ ተግባር ተከናውኗል  ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ትምህርት ማህበረሰቡ የፋይዳ ዲጂታል ትግበራ በትምህርት ቤቶች ውጤታማ እንዲሆን ያከናወነውን ተግባር በተሞክሮነት ወደ ክልሎች የማስፋት ስራ እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት የዲጂታል አገልግሎቱን ለማሳለጥና ጠንካራ የሆነ የማንነት አስተዳደር  ስርዓት ለመፍጠር እያገዘ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም