በዘንድሮ የመኸር ወቅት እስከ አሁን 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በዘንድሮ የመኸር ወቅት እስከ አሁን 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 6/2017(ኢዜአ)፦በ2017/18 የመኸር ወቅት እስከ አሁን 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
በግብርናው ዘርፍ በመኸር፣ በበልግ እንዲሁም በመስኖ ልማት ስራዎች ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ሥራዎች አመርቂ ውጤቶች መመዝገቡን አስታውሰዋል።
በዚህ ዓመት በመላ አገሪቱ 21 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመኸር እርሻ በተለያዩ ሰብሎች ዘር እንደሚሸፈን ገልጸዋል።
አሁን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የዘር ስራ የሚከናወንበት በመሆኑ እንደ በቆሎ ያሉ የአገዳ ሰብሎች ቀድሞ መዘራታቸውን ጠቁመው፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስና ሌሎች እንደየ አካባቢው ሥነ-ምህዳር እየተዘሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እና ለአርሶ አደሩ ግንዛቤ በመፍጠር ጭምር በመሰራቱ በዚህ ዓመት የተሻለ ምርት ይጠበቃል ብለዋል።
ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያችሉ የአፈር ማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘር እና የተለያዩ ግብዓቶች ለአርሶ አደሩ በወቅቱ እንዲደርሱ መደረጉንም ተናግረዋል።
የመኸር የእርሻ ጊዜ ለኢትዮጵያ ትልቁ የምርት ጊዜ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ በዓመቱ በአጠቃላይ ከሚመረተው ምርት 70 በመቶ የሚሆነው በዚሁ ወቅት የሚለማ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ እንደገለጹት ዘንድሮ 13 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም የሚለማ ሲሆን ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር እድገት ማሳየቱን ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ በኩታ ገጠም በሚሰራበት ወቅት ምርታማነቱ የበለጠ እንደሚጨምር አስታውሰው ይህም የበለጠ መጠናከር እንዳለበት አስታውቀዋል።
6 ሚሊየን ሄክታር መሬት በመካናይዜሽን የታረሰ መሆኑን ገልጸው ይህም ከባለፈው በ1 ሚሊየን ሄክታር መሬት ብልጫ እንዳለው ጠቅሰዋል።
የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ትልቁ ለውጥ የአርሶ አደሮች የቴክኖሎጂን መጠቀም ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመኸር ወቅት 21 ሚሊየን ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን ከ659 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል።