አሰባሳቢ ትርክትን በሚያሰርጹ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት መጠናከር ሚናችንን እናጎለብታለን- ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
አሰባሳቢ ትርክትን በሚያሰርጹ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት መጠናከር ሚናችንን እናጎለብታለን- ወጣቶች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 6/2017(ኢዜአ)፦ አሰባሳቢ ትርክትን በሚያሰርጹ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት መጠናከር የሚጠበቅብንን ድርሻ ይበልጥ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ማህበር አባላት ተናገሩ።
አሰባሳቢ ትርክትን በመገንባት ሂደት ወጣቶች እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ በተመለከተ ኢዜአ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ማህበር አባላትን አነጋግሯል።
ወጣት አቤል ኃይሉ በሰጠው አስተያየት እንደገለጸው፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግስት የወጣቱን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን በስፋት አከናውኗል።
በተለይም በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የወጣቱ ተሳትፎ እንዲጎለብት በማድረግ አካታች የስራ ፈጠራና እድል ተጠቃሚነት፣ በሰላም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ፣ በግብርና እና በሌሎች ዘርፎች ወጣቱን ያማከለ ስራ መከናወኑን ገልጿል።
ይህም ወጣቱ የማህበረሰብ ክፍል በአገሩ የትኛውም ጉዳይ ላይ በባለቤትነትና በሃላፊነት እንዲሳተፍ የሚያነሳሳ ከመሆኑም ባሻገር በአገር ሁለንተናዊ ልማት ላይ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ነው ያለው።
የዚህ ዘመን ትውልድ የራሱን አሻራ ከሚያኖርበት ተግባራት አንዱ የጋራ አሰባሳቢ ትርክትን ማስረጽ መሆኑን ጠቅሶ፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያንን በጋራ ሊያሰባስቡ የሚችሉ በርካታ ተግባራት መኖራቸውን አብራርቷል።
በመሆኑም አሰባሳቢ ትርክትን በሚያሰርጹ ተግባራት ላይ በመሳተፍ የአገረ መንግስት ግንባታው ሂደት አካል ለመሆን የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እየተወጣ መሆኑን ተናግሯል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወጣት መልካም በንቲ በበኩሏ እንደገለጸችው፤ ወጣቱ ጊዜውን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ከራሱ አልፎ አገሩን የሚያገለግልበትን እድል በማመቻቸት ረገድ መንግስት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን አከናውኗል።
ለአብነትም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወጣቱ ማህበረሰቡንና አገሩን በቅንነት እንዲያገለግልና ለመልካም ተግባር በጋራ እንዲሰባሰብ እድል ፈጥሯል ነው ያለችው።
ይህም አገሩን የሚወድ ፣ለማህበረሰቡና ለአገሩ ተቆርቋሪና መልካም ስነ-ምግባር ያለው ትውልድ እንዲፈጠር በማድረግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ወጣቱ ትውልድ አገርን እየሰራ ለቀጣዩ ትውልድ ማሻገር የሚጠበቅበት መሆኑን በመጠቆም፤ አሰባሳቢ ትርክትን ማስረጽና በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅበታል ብላለች።
በመሆኑም እንደ አገር የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ወደ እድል በመቀየር ወጣቱ ለአገረ መንግስት ግንባታው ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ነው ያለችው።
ወጣት መሰረት ሙልዬ እንዲሁ ወጣቱ በአሰባሳቢ ትርክት ዙሪያ ያለው አዎንታዊ አመለካከት እየዳበረ መምጣቱን ገልጻለች።
ይህም አብሮነትን የሚያጎለብትና የዜጎችን የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን ገልጻ፤ ወጣቱ የገዢ ትርክት እሳቤዎችን መገንዘብና ማስፋት ይጠበቅበታል ብላለች።