ሞሮኮ እና ዛምቢያ ለሩብ ፍጻሜ አለፉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ በ13ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ አንድ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ማምሻውን ተደርገዋል።

በፕሪንስ ሙላይ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አዘጋጇ ሞሮኮ ሴኔጋልን 1 ለ 0 አሸንፋለች።

ያሲን ምራቤት በመጀመሪያ አጋማሽ ጭማሪ ደቂቃዎች ላይ በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠረችው ግብ ቡድኑን ባለድል አድርጋለች።

ሞሮኮ በሰባት ነጥብ የምድቡ መሪ ሆና በማጠናቀቅ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅላለች።

በዚሁ ምድብ ማምሻውን በተመሳሳይ ሰዓት በኤል ባቺር ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ ዛምቢያ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን 1 ለ 0 ረታለች።

ራቼል ኩንዳናንጂ የማሸነፊያውን ጎል በ9ኛው ደቂቃ አስቆጥራለች።

የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የአጥቂ መስመር ተሰላፊ ፋሎኔ ፓምባኒ በ69ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብታለች።

ውጤቱን ተከትሎ ዛምቢያ በተመሳሳይ ሰባት ነጥብ በሞሮኮ በግብ ክፍያ ተበልጣ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ሩብ ፍጻሜ ገብታለች።

በምድቡ ሶስቱንም ጨዋታ የተሸነፈችው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ከውድድሩ የተሰናበተች የመጀመሪያ ሀገርም ሆናለች።

በምድብ አንድ በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ይዛ የጨረሰችው ሴኔጋል ምርጥ ሶስተኛ ሆኖ ለማለፍ የሌሎች ምድብ ውጤቶችን ትጠብቃለች።

ናይጄሪያ ሩብ ፍጻሜ የገባች የመጀመሪያ ሀገር መሆኗ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም