በሲዳማ ክልል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር እርስ በእርስ የመደጋገፍ ባህል እንዲጎለብት አግዟል - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር የህብረተሰቡን እርስ በእርስ የመደጋገፍ ባህል እንዲጎለብት ማገዙን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለፁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ‎የክልሉን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በምስራቃዊ ሲዳማ ዞን ዳዬ ከተማ አስጀምረዋል።


 

አቶ ደስታ ‎አገልግሎቱን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በህብረተሰቡ ውስጥ የመደጋገፍ ባህል እንዲጎለብት አግዟል።

‎በአገልግሎቱ ወጣቶች፣ የመንግስት ተቋማት፣ ሠራተኞች፣ ባለሀብቶችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውንና በልማት ስራውም በርካታ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

‎ለአብነትም ባለፈው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ3ሺህ በላይ ቤቶችን በማደስና በአዲስ መልክ መገንባት ለብዙዎች እፎይታ መስጠት መቻሉን ጠቅሰዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መኖሪያ ቤታቸው የሚገነባላቸው አቅመ ደካሞች ኑሯቸውን በዘላቂነት ለማሻሻል ቋሚ የገቢ ማስገኛ ሥራ ይፈጠርላቸዋል ብለዋል።

‎የክልሉ ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ እመቤት ኢሳያስ በበኩላቸው በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ ወጣቶችን በማሳተፍ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ነው ያሉት።


 

በአገልግሎቱ 800ሺህ ወጣቶችን በማሳተፍ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ‎የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤት መልሶ መገንባት፣ ደም መለገስ፣ ማዕድ ማጋራት፣ ትምህርትና ችግኝ ተከላን ጨምሮ በ14 መስኮች ወጣቶችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ ብለዋል።

ከተሳታፊ ወጣቶች መካከል የዳዬ ከተማ ነዋሪ ወጣት ለማ ለገሰ በየዓመቱ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በንቃት መሳተፉ ውስጣዊ እርካታን እንደሚሰጠው ተናግሯል።

‎በተለይ በሰብአዊ የድጋፍ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ የአቅመ ደካሞችን ማህበራዊ ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረጉ ደስተኛ መሆኑን ገልጿል።


 

‎‎ቤታቸው በአዲስ መልክ ግንባታ ከተጀመረላቸው ነዋሪዎች መካከል ከአራት ልጆቻቸው ጋር የሚኖሩት ወይዘሮ እታፈራሁ እርገጤ በበጎ ፈቃደኞች በአዲስ መልክ የቤታቸው ግንባታ በመጀመሩ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸውም ተናግረዋል።

‎በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ በየነ በራሳ፣ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችና የሚመለከታቸው አካላት የተገኙ ሲሆን የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሀግብርም ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም