ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው የጤና ተቋማት ማጠናከር ስራ ላይ በመሳተፍ ድጋፍ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው የጤና ተቋማት ማጠናከር ስራ ላይ በመሳተፍ ድጋፍ እያደረገ ነው

ሆሳዕና ፤ ሐምሌ 5/2017 (ኢዜአ):- ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢው የሚገኙ የጤና ተቋማት ማጠናከር ስራ ላይ በመሳተፍ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ተገለጸ ።
ዩኒቨርሲቲው በሀድያ ዞን በሆመቾ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ያስገነባውን ሞዴል የማህበረሰብ መድሃኒት ቤት አስመርቆ ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዳዊት ሀየሶ (ዶ/ር) እንዳሉት ፤ ተቋሙ ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ነው።
በአካባቢው የሚገኙ የጤና ተቋማት ያሉባቸውን የህክምና ግብዓትና ሌሎች ቁሳቁሶችን አሟልተው የተሻለ የህክምና አገልግሎት እንዲሰጡ እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከ12 ሚሊየን ብር በላይ በጀት በመመደብ በአካባቢው የሚገኙ 4 የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎችን የመድኃኒት አቅርቦት ችግር ለማቃለል የማህበረሰብ መድሀኒት ቤቶችን በመገንባት የማስረከብ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡
የሀድያ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ተወካይ የሆኑት አቶ ሚሻሞ ወርቅነህ በበኩላቸው፤ በዞኑ የሚገኙ የህክምና ተቋማት ያለባቸውን የመድኃኒት አቅርቦት ችግር ለማቃለል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ተገንብቶ ዛሬ ለአገልግሎት የበቃው የማህበረሰብ መድሀኒት ቤት የዚህ ጥረት አካል እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የሆመቾ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ምስጋና አለሙ ፤ ዛሬ ለአገልገሎት የበቃው የማህበረሰብ መድሃኒት ቤቱ በሆስፒታሉ የተሟላ የህክምና አገልግሎት ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝ ነው የገለጹት፡፡
በመርሐ ግብሩ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የችግኝ ተከላ ያከናወኑ ሲሆን፤ በዚህም የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡