በክረምት በተከታተልነው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስልጠና የቀሰምነው ዕውቀት በትምህርት ቤት ውጤታማ እንድንሆን አግዞናል - ኢዜአ አማርኛ
በክረምት በተከታተልነው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስልጠና የቀሰምነው ዕውቀት በትምህርት ቤት ውጤታማ እንድንሆን አግዞናል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የታዳጊዎች የክረምት ስልጠና የቀሰሙት ዕውቀት በትምህርት ቤት ውጤታማ እንዲሆኑ እንዳገዛቸው ቀደም ሲል የሰው ሰራሽ አስተውሎት(ኤ አይ) ስልጠና የተከታተሉ ታዳጊዎች ገለፁ።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በተለያዩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች አራተኛውን የታዳጊዎች የክረምት ስልጠና በሳይንስ ሙዚየም አስጀምሯል።
ስልጠናውን ተከታትለው የጨረሱ ታዳጊዎች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ ቀደም ሲል የወሰዱት ስልጠና ህልማቸውን እውን ለማድረግ በሚሰሩት ስራ በብዙ መንገድ ደግፏቸዋል።
በትምህርት ማዘመን የሚያስችል ፕሮጀክት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው ወጣት ሰለሞን መብሬ የ2014 የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስልጠና ወስዶ አጠናቋል።
እንደወጣት ሰለሞን ገለጻ፤ አሰልጣኞቹ በዘርፉ ያላቸው እውቀት ከፍተኛ በመሆኑ ፈጠራን ለመውደድና ለማሰብ አስችሏቸዋል።
በዚህም የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ወደ ጥቅም መቀየር የሚያስችል አቅም ማዳበራቸውን ጠቁሞ፤ በተለይ በቡድን የመስራት መንፈስ እንዲላበሱ እንደረዳቸው ተናግሯል።
የ12ኛ ክፍል ተማሪ ዲቦራ ወንድወሰን የ2015 የሰው ሰራሽ አስተውሎት የክረምት ስልጠና ተመራቂ ነች።
በተከታተለቸው ስልጠና በአጭር ጊዜ ውስጥ አዳዲስ ነገሮች ለመገንዘብ መቻልዋን ተናግራለች።
እንዲሁም በቡድን የመስራት ችሎታና ችግሮችን የመፍታት አቅም ለማዳበር እንደረዳትም ነው የገለፀችው።
አስተያየት ሰጪዎቹ ስልጠናው የሀገር ብሎም የማህበረሰብ ችግር መፍታት የሚያስችሉ መርሃ ግብሮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በዚህም የአራተኛውን ዙር የሰው ሰራሽ አስተውሎት(ኤአይ) የክረምት ስልጠና የሚወስዱ ታዳጊ ተማሪዎች ያገኙትን እድል በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል ብለዋል።
በሌላ በኩል ዘንድሮ ወደ ስልጠናው የሚገቡ ሰልጣኞች በበኩላቸው፤ በስልጠናው የተሻለ እውቀትና ችሎታ አዳብረው ለመውጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ተማሪ ቅዱስ ሙሴ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት(ኤአይ) መማር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በማመን ወደ ስልጠናው መምጣቱን ተናግሯል።
ታዳጊዎች እንደዚህ ዓይነት ስልጠናዎች መሳተፋቸው ትልቅ ህልም እንዲያልሙ ና ህልማቸውን በተጨባጭ በመተርጎም ከራሳቸው አልፈው ለሀገር እንዲተርፉ ይረዳል ብሏል።
የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ኑሃሚን ጥበቡ እንደምትናገረው፤ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ስራዎችን ቀለል ባለ መልኩ ለማከናወን የሚረዳ በመሆኑ ሥልጠናውን ለመከታተል ፍላጎት አሳድሮባታል።
በዚህም ዘንድሮ በሚሰጠው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የክረምት ስልጠና በምታገኘው እውቀት ፓይለት የመሆን ህልሟን እውን ለማድረግ እንደሚያግዛት ታምናለች።