በሁሉም ኢንዱስትሪ ፓርኮች የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የማከናወኑ ተግባር ይጠናከራል - ሚኒስትር መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
በሁሉም ኢንዱስትሪ ፓርኮች የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የማከናወኑ ተግባር ይጠናከራል - ሚኒስትር መላኩ አለበል

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ በሀገሪቱ በሚገኙ ሁሉም ኢንዱስትሪ ፓርኮች የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የማከናወኑ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሩና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ የስራ እንቅስቃሴን የተመለከቱ ሲሆን፤ ችግኝ በመትከልም አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል፡፡
በዚህ ወቅት ሚኒስትሩ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተቀናጁ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከአየር ንብረት ጋር የተስማማ ሁኔታ እንዲኖር የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ ስራ እየተስፋፋ ነው።
ዛሬም በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተከናወነው የዚህ አካል መሆኑን አንስተው፤ በቀጣይም ይህንን የበለጠ እያጠናከርን እንሄዳለን ብለዋል።
ጠንክሮ በመስራትና ኢኮኖሚኖዋን በማሻሻል ኢትዮጵያ እንደምታንሰራራ ያመለከቱት ሚኒስትሩ፤ የምንተክለውም መልካም ዘር ነው፤ የኢትዮጵያን የወደፊት ተስፋን የሚያለምለምና የስራ ባህልን ታሳቢ ያደረገ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
"በመትከል ማንሰራራት" የሚለው ቁልፍ መልዕክትም እነዚህን ሁሉ ያየዘ በመሆኑ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢንዱስትሪዎች የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ሀይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ሁሉ ስራ የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የችግኝ ተከላ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል፡፡
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሩ የሚተከለው ችግኝ ለምግብነት፣ ለፋብሪካ ግብዓትና ለማገዶ ጨምሮ አካባቢው ለኑሮና ለስራ የተመቸ ከማድረግ ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቅሰው፤ ፓርኮች ይህን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አብራርተዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ቦርድ ሰብሳቢ አራርሶ ገረመው(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተሰማሩ ከ8 በላይ ካምፓኒዎች የግብርና ምርቶች በማቀነባበር ላይ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
ፓርኩን ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችል የድጋፍና ክትትል ውይይት መደረጉን ተናግረው፤ ችግኝ በመትከል የፓርኩን ስራ ለማጠናከር የሚያግዝ ዐሻራ ማኖራቸውንም አንስተዋል፡፡
በፓርኩ የስራ ዕድልና የገበያ ትስስርን በመፍጠር እንዲሁም የግብርና ቴክኖሎጂ በማሸጋገር ረገድ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ መኖሩን የገለጹት የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሀይሉ ዬተራ ናቸው፡፡
ከ137ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የምርት አቅርቦት ትስስር መፈጠሩንም ጠቅሰዋል፡፡