"ዙሪያ" የተሰኘው መተግበሪያ የንግድ ስርዓቱን በማቀላጠፍ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ጉልህ ሚና ይኖረዋል - ኢትዮ ቴሌኮም - ኢዜአ አማርኛ
"ዙሪያ" የተሰኘው መተግበሪያ የንግድ ስርዓቱን በማቀላጠፍ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ጉልህ ሚና ይኖረዋል - ኢትዮ ቴሌኮም

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ "ዙሪያ" የተሰኘው መተግበሪያ የንግድ ስርዓቱን በማቀላጠፍ፣ የተገልጋዮችን ጊዜና ገንዘብ በመቆጠብ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ሞባይል መኒ ቢዝነስ ኦፊሰር ብሩክ አድሃና ገለጹ።
ኢትዮ ቴሌኮም፣ ዳሽን ባንክ እና ኢታ ሶሊዩሽን የንግድ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን የሚያቀላጥፍ "ዙሪያ" የተሰኘ የቢዝነስ አውቶሜሽን ሶሉሽን መተግበሪያ ይፋ አድርገዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ችፍ ሞባይል መኒ ቢዝነስ ኦፊሰር ብሩክ አድሃና እንዳሉት፣ መተግበሪያው የንግድ ስርዓቱን በማዘመን የተገልጋዮችን ጊዜና ገንዘብ የሚቆጥብ ነው።
የፋይናንስ እንቅስቃሴውን በቀላሉ ለማወቅ እንደሚረዳና ለነጋዴዎች የተሻለ የክፍያ መፈጸሚያ አማራጭ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
"ዙሪያ" ለአጠቃቃቀም ቀላል እና ፈጣን፣ ደህነንቱ የተረጋገጠ መሆኑንም ጨምረው አንስተዋል።
የውጪ እና የሀገር ውስጥ የክፍያ ካርዶችን እንደሚቀበልና የሂሳብ ስራን ቀላል እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።
በወረቀትና በማሽን ይሰራ የነበረውን የክፍያ ስርዓት ወደ አንድ ወጥ አተገባበር የሚያመጣ መተግበሪያ እንደሆነም ጠቁመዋል።
መተግበሪያው የንግድ ስርዓቱንና አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።