ወጣቶች ለወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስኬታማነት የድርሻቸውን ይወጣሉ - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች ለወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስኬታማነት የድርሻቸውን ይወጣሉ

ድሬዳዋ፣ ሐምሌ 5/2017 (ኢዜአ)፡- ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አንድነትንና መተጋገዝን ስለሚያጎለብት ለስኬታማነቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በድሬዳዋ በአገልግሎቱ እየተሳተፉ ያሉ ወጣቶች ገለጹ።
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የሚመራው የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተሳታፊዎች ዛሬ በድሬዳዋ የጽዳት ዘመቻ አካሂደዋል።
በአገልግሎቱ የተሳተፉ ወጣቶች ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት በመሳተፍ የዜጎችን ማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ተሳታፊዎች መካከል ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የመጣችው ወጣት ሃና፤ ለበጎ ተግባር ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ ወጣቶች መሰባሰባቸውን ገልጻ ይህም የባህል ትውውቅ ለማድረግና አንድነትን ለማጠናከር እንደሚያግዛቸው ተናግራለች።
በድሬዳዋ በሚኖራት ቆይታም በጽዳት ሥራ፣ በችግኝ ተከላና በደም ልገሳ መርሀግብሮች በመሳተፍ የበኩሏን ለመወጣት መዘጋጀቷን ተናግራለች።
ህዝብን ባሳተፈ መንገድ ሀገርን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የድርሻውን ለመወጣት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት መሳተፉን የገለጸው ደግሞ የኢሉአባቦር ዞን ነዋሪ ወጣት ባጫ ነመራ ነው።
ለበጎ ፈቃድ ሥራው ወደ ተለያዩ ክልሎች በተጓዘበት ወቅት ያየው ብዝሀ ወግና ባህል ኢትዮጵያን በተሻለ ለማወቅ እንዳስቻለውም ተናግሯል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ተሳትፎና አደረጃጀት አቅም ግንባታ ዴስክ ኃላፊ አቶ አድነው አበራ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ "በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መርህ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለአራተኛ ጊዜ በመላው ኢትዮጵያ እየተካሄደ ይገኛል።
ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እያቃለለ ከመምጣቱ ባሻገር የባህል ትውውቅን እያጎለበተ መሆኑንም ተናግረዋል።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ትውልዱ በቅብብሎሽና በመተጋገዝ የነገዋን ኢትዮጵያ ለመገንባት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርለት ገልጸው፣ በልማት ስራውም አዲሱ ትውልድ ሀላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ካሊድ መሐመድ በበኩላቸው፣ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ወሰን ተሻጋሪ ወጣቶች ድሬዳዋ ተገኝተው ላበረከቱት አርአያነት ያለው ተግባር አመስግነዋል።
በመረሀ ግብሩም በ14 የልማት መስኮች በገጠርና በከተማ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።