የገጠር ኮሪደር ልማት የኅብረተሰቡን ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ትልቅ ኢኒሼቲቭ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የገጠር ኮሪደር ልማት የኅብረተሰቡን ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ትልቅ ኢኒሼቲቭ ነው

ሚዛን አማን፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ የገጠር ኮሪደር ልማት የኅብረተሰቡን ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ትልቅ ኢኒሼቲቭ መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮችና ሴክተር ክትትል ሚኒስትር ዴኤታ አክሊሉ ታደሰ ገለጹ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና ተጠሪ ተቋማት በቤንች ሸኮ ዞን የገጠር ኮሪደር ልማትን እሳቤ አሟልተው የሚገነቡ አምስት ሞዴል ቤቶች ግንባታ ሥራን አስጀምረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮችና ሴክተር ክትትል ሚኒስትር ዴኤታ አክሊሉ ታደሰ እንዳሉት የገጠር ኮሪደር ልማት እሳቤ የገጠር ነዋሪዎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ትልቅ ሀገራዊ ኢኒሼቲቭ ነው።
በዚህም ለአርሶ እና አርብቶ አደሩ ጤናማና ምቹ የአኗኗር ስርአት ከመፍጠር ባለፈ ከምርታማነት ጋር ለማስተሳሰር ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የሞዴል ቤቶች ግንባታ ጽዳቱን የጠበቀ መኖሪያ ቤት ከመገንባት ጀምሮ የሌማት ትሩፋት፣ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የአረንጓዴ ሥፍራና ለማኅበራዊ አገልግሎት የሚውሉ መስኮችን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለዚህም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የገጠር ኮሪደር እሳቤን ታሳቢ ያደረጉ አምስት ሞዴል ቤቶችን በጉራፈርዳ ወረዳ እንደሚገነባና ከእዚህም ሌሎች አይተው እንዲያስፋፉ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።
የገጠር ኮሪደር ልማት ተግባር የገጠር ነዋሪዎች አኗኗርን ዘመናዊ በማድረግ ለብልጽግና ጉዞ ትልቅ መሠረት የሚጥል መሆኑንም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የተናገሩት።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) በበኩላቸው መንግስት የከተማና የገጠር ነዋሪዎችን ያማከለ የልማት ኢኒሼቲቮችን በመዘርጋት ሁሉንም ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ ነው ብለዋል።
በክልሉ የተለያዩ ቀበሌዎች የተጀመሩ የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸው፣ ልማቱንም በምግብ ራስን ለመቻል ከሚሰራው ሥራ ጋር ማቆራኘት እንደሚገባ ገልጸዋል።