በመዲናዋ በ2018 በጀት ዓመት ለሰው ተኮር እና ድህነት ቅነሳ የልማት ስራዎች ትኩረት ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2018 በጀት ዓመት የሰው ተኮር እና የድህነት ቅነሳ የልማት ስራዎችን ለማጠናከር ትኩረት መስጠቱን አስታወቀ።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ አብዱልቃድር ሬድዋን የከተማ አስተዳደሩን የ2018 በጀት ዓመት ዝርዝር የበጀት መግለጫ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።


 

የ2018 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች፣ የኮሪደር ልማትና አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ የቤት ልማት ግንባታን የበለጠ በማጠናከር በአስር ዓመት መሪ የልማት እቅድና በሁለተኛው የአምስት ዓመት የተቀመጡ ስትራቴጂክ ግቦችን ማሳካት ማዕከል ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

በዚህም በ2017 የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ማጠናቀቅ፣ ነባርና አዳዲስ የመኖሪያ ቤት ግንባታዎችን ማጠናቀቅ፣ የከተማዋን የቱሪስት መዳረሻነት የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶችን ማስፋት ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።

እንደ ቢሮ ሃላፊው ገለጻ፤ ሰው ተኮርና ድህነት ቅነሳ ላይ ያተኮሩ የልማት ስራዎችን ማጠናከርና ሌሎች በበጀት ዓመቱ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው።

ይህንንም የልማት እቅድ ለማሳካት በ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ 350 ነጥብ 13 ቢሊዮን ብር በጀት መያዙን ገልጸዋል።

ለ2017 በጀት ዓመት ከጸደቀው የወጪ በጀት አንጻር የዘንድሮው 108 ነጥብ 83 ቢሊዮን ብር ጭማሪ እንዳለው ተናግረዋል።

ለበጀቱም ከታክስ ገቢ 238 ነጥብ 93 ቢሊዮን ብር፣ ታክስ ካልሆኑ ምንጮች 46 ቢሊዮን ብር፣ ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች 56 ነጥብ 24 ቢሊዮን ብርና ከሌሎችም ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል።

የካፒታል በጀት የከተማ አስተዳደሩ የትኩረት አቅጣጫ ለሆኑ የቤት፣ የኮሪደር ልማትና ሌሎች ሰው ተኮር ለሆኑ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ለማዋል ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል ነው ያሉት።

የምክር ቤት አባላት ከተማ አስተዳደሩ አጠቃላይ ለ2018 የያዘው በጀት በከተማዋ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በመፈጸም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ አንስተዋል።

አባላቱ ከሥራ ዕድል ፈጠራና ከመስሪያ ቦታ ግንባታ ጋር በተገናኘ ትኩረት ማግኘት አለባቸው በሚል ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የቢሮው ሃላፊው፥ በበጀት ዓመቱ ለስራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ ሚና ላላቸው ዘርፎች ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት የቀረበውን የበጀት ውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አጽድቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም