ከሀገር በቀል እፅዋት ለእንስሳት ህክምና የሚያገለግሉ መድሃኒቶችን በምርምር የማፍለቅ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ ሀገር በቀል እፅዋትን በመጠቀም ለእንስሳት ህክምና የሚያገለግሉ መድሃኒቶችን የማፍለቅ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ ገለጹ።

የኢንስቲትዩቱ አመራሮች በእንስሳት ጤና እና ተያያዥ የምርምር ዘርፍ አዳዲስ የእንስሳት መድሃኒቶችና የመመርመሪያ ማሳያ ስራዎችን በተመለከተ በሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል የመስክ ምልከታ አካሂደዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ፥ ኢትዮጵያ ያላት ሰፊ የእንስሳት ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ አልዋለም ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ ኢትዮጵያ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ፤ የእንስሳት በሽታን መከላከል የሚያስችሉ ምርምሮችንና ተያያዥ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከልም በምርምር የተደገፉ የተለያዩ የመኖ ዝርያዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለእንስሳት ጤና ተገቢውን ትኩረት በመስጠት በእንስሳት ጤና ዙሪያ በርካታ የምርምርና የህክምና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ሀገር በቀል እጽዋት ላይ ተገቢውን ምርምር በማድረግ የእንስሳትን ጤና መጠበቅ የሚያስችሉ መድሃኒቶችንና ኬሚካሎችን በምርምር እያፈለቀ እና ወደ ጥቅም እየቀየረ መሆኑንም ተናግረዋል።

የብሔራዊ የእንስሳት ጤና ምርምር አስተባባሪ ዶክተር ቤክሲሳ ኡርጌ፥ በእንስሳት ቆዳ ላይ የሚከሰቱ በሽታዎችን ማከም የሚያስችሉ መድሀኒቶች እና ኬሜካሎች በምርምር መገኘታቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ እነዚህን የምርምር ውጤቶች ወደ ማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል እውቅና ከሚመለከተው ተቋም ለማግኘት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ተወካይ ዶክተር ድሪባ ሁንዴ፥ ማዕከሉ የእንስሳት ዝርያን ከማሻሻል ባለፈ የእንስሳት ጤናን መጠበቅ የሚያስችሉ የጥናትና የምርምር ስራዎች እያከናወነ ነው ብለዋል።

ማዕከሉ በአካባቢው በእንስሳት እርባታ ዘርፍ ለተሰማሩ ዜጎች የተሻሻሉ እንስሳት ዝርያዎችን እንዲያገኙ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሆለታ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ከበደ ስለሺ ናቸው።

የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በማዕከሉ እየተተገበሩ ለሚገኙ የምርምር ስራዎች ከተማ አስተዳደሩ ተገቢውን እገዛ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡

የመስክ ተሳታፊ አመራሮች በማዕከሉ ግቢ አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም