ስርዓተ ምግብ ምንድን ነው? - ኢዜአ አማርኛ
ስርዓተ ምግብ ምንድን ነው?

ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
ዓለም አቀፍ ሁነቱን ኢትዮጵያ እና ጣልያን በጋራ ያዘጋጃሉ።
የስርዓተ ምግብ ሽግግር እና ትራንስፎርሜሽን ጉባኤው የሚያጠነጥንበት አበይት አጀንዳ ነው።
ለመሆኑ ስርዓተ ምግብ ሲባል ምን ማለት ነው? የሚለውን ጉዳይ እንመልከት።
ስርዓተ ምግብ(Food System) የምግብ ማምረት፣ ማቀነባበር፣ ማሰራጨት፣ መጠቀም እና ማስወገድ ውስጥ ያሉ ሂደቶችና ተግባራትን አጠቃሎ የያዘ ሀሳብ ነው።
ህዝብን በመመገብ ውስጥ ሚና ያላቸው ሰዎች፣ ፀጋዎች፣ ተቋማትና መሰረተ ልማቶችን ያካትታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር "ከራዕይ ወደ ተግባር፤ የኢትዮጵያ ዘላቂና አካታች የምግብ ስርዓት ሽግግር ጉዞ" በሚል መሪ ሀሳብ ዓበይት ትኩረቱን በኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብ ላይ ያደረገ ውይይት ሐምሌ 3 ቀን 2017 ዓ.ም አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር) በምግብ ስርዓት ሽግግር ከምርት እስከ ተጠቃሚ ባለው ሰንሰለት ውስጥ ሁሉን አቀፍ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
በስርዓተ ምግብ ሂደት ውስጥ ካሉ ጉዳዮች አንዱ እንኳን ቢጓደል ሂደቱ ምሉዕ እንደማይሆንም ገልጸዋል።
ምርት እርሻ፣ የአሳ ምርት፣ የከብት እርባታ እና የተለያዩ የምግብ አመራረት አይነቶችን ያካተተ ነው።
ማቀነባበር ጥሬ ምግብን ጥቅም ላይ ወደሚውሉ ምርቶች የመቀየር ሂደት ሲሆን ስርጭት ትራንስፖርት፣ የመጋዘን ክምችትና ገበያ ማድረስን በስሩ ይዟል።
መጠቀም በሚባለው ደረጃ ምግብ መግዛት እና መብላት ነው።
በምግብ እሴት ሰንሰለት ውስጥ የምግብ ጥራትና ብዛት ጥራት መቀነስ፣ የሚጣሉ ትራፊ ምግቦች አስተዳደርና የምግብ ተረፈ ምርቶችን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) መቀየር የመጨረሻው የስርዓተ ምግብ ሂደት መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
የኢኮኖሚ ስርዓት፣ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ የመንግስት ፖሊሲዎች፣ የከባቢ አየር ሁኔታ እንዲሁም ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን በስርዓተ ምግብ ውስጥ ያላቸው ሚና ወሳኝ ነው።
ስርዓተ ምግብ ሁለንተናዊ እና ሁሉን አቀፍ መሆኑ በኢትዮጵያ ዘላቂና አካታች የምግብ ስርዓት የሽግግር ጉዞ እውን እንዲሆን ትልቅ ጠቀሜታም አለው።