ኢጋድ ለአህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ በቁርጠኝነት መስራቱን ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ተፈጻሚነት በቁርጠኝነት መስራቱን እንደሚቀጥል የተቋሙ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) ገለጹ።

47ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት እና 7ኛው የህብረቱ ቀጣናዊ ማህበረሰቦች የመንፈቅ ዓመት የጋራ የትብብር ስብሰባ በኢኳቶሪያል ጊኒ ማላቦ እየተካሄደ ይገኛል።


 

በተጓዳኝም ሶስተኛው በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ ላይ ያተኮረ የቀጣናዊ ማህበረሰቦች ኃላፊዎች የጋራ ስብሰባ ተካሂዷል።

ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ትስስር፣ የንግድ ልውውጥና የፖሊሲ ተጣጣሚነትን በመፍጠር የአፍሪካን የኢኮኖሚ ትስስር እውን በማድረግ ያላቸው ቁልፍ ሚና በስብሰባው ተነስቷል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) በስብሰባው ስለ ኢጋድ ቀጣናዊ የመሰረተ ልማት ማስተር ፕላን ያነሱ ሲሆን ማዕቀፉ ከአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና እና አጀንዳ 2063 ጋር የሚመጋገብ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢጋድ ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ በቁርጠኝነት መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ኢዜአ ከተቋሙ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም