ቀጥታ፡

ወጣቶች ለሀገር ልማት እና ሰላም ሚናቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - ሼኽ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ ወጣቶች ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት እያደረጉት ያለውን አስተዋፅኦ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼኽ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ አስገነዘቡ።

በአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የአዲስ አበባ ሙስሊም ወጣቶች ሊግ 3ኛ ዓመት 2ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ምክር ቤቱ ሙስሊሙን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል።

ወጣቶች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በጎ ሚና እየተጫወቱ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሙስሊም ወጣቶች ሊግም ባለፉት ሶስት ዓመታት በበጎ ፈቃድ ተግባራት ሲያደርገው የነበረውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም ወጣቶች ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ እንዲያጠናክሩም አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼኽ ሱልጣን አማን ኤባ በበኩላቸው፤ የሙስሊም ወጣቶች ሊግ ከተደራጀ ጀምሮ ከፍተኛ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ ሊጉ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ምክር ቤቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመጥቀስ።

የአዲስ አበባ ሙስሊም ወጣቶች ሊግ ፕሬዝዳንት ሙሀመድ አህመድ፥ ሀገራዊ ለውጡ ለወጣቶች የተሳትፎና የተጠቃሚነት ዕድልን ማስፋቱን ገልጿል።

የአዲስ አበባ ሙስሊም ወጣቶች ሊግ ባለፉት ሶስት ዓመታት አቅመ ደካሞችን ማገዝን ጨምሮ ማህበራዊ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቅሶ፥ በቀጣይም ይህን ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል።

የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል ፕሬዝዳንት ኡስታዝ ሀይደር ከድር በበኩሉ፤ ሊጉ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ትላልቅ ተግባራት ማከናወኑን ገልጿል።

ወጣቶች አብሮነታችንን በማጠናከር ለሀገር እድገት ሚናችንን ማሳደግ አለብን ሲልም መልዕክት አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም