አረንጓዴ ዐሻራ የነገዋን ኢትዮጵያ ለትውልዱ ምቹና የተሻለች የሚያደርግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ ዐሻራ የነገዋን ኢትዮጵያ ለትውልዱ ምቹና የተሻለች የሚያደርግ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ አረንጓዴ ዐሻራ የነገዋን ኢትዮጵያ ለትውልዱ ምቹና የተሻለች የሚያደርግ መሆኑን የነገዋ የሴቶች ተሀድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ሰልጣኞች እና የባለድርሻ ተቋማት ኃላፊዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ማስጀመራቸው ይታወቃል፡፡
የነገዋ የሴቶች ተሀድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ሃላፊዎች፣ ሰልጣኞች እና ባለድርሻ አካላት በማዕከሉ ግቢ አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።
የቀድሞ የአዲስ አበባ ማኅበራዊ ትረስት ፈንድ ዋና ዳይሬክተር አስራት ንጉሤ በዚሁ ወቅት፤ አረንጓዴ ዐሻራ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ከመከላከል ጀምሮ በርካታ ትሩፋቶችን እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይም በነገዋ የሴቶች የተሃድሶና የልህቀት ማዕከል የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር መከናወኑ ትልቅ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።
በማዕከሉ ያሉ ሴቶች ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡና ዐሻራቸውን የሚያሳርፉበት እድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በስልጠና ቆይታቸው ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ ስለአረንጓዴ ልማት ተግባራዊ ግንዛቤ እንደሚያገኙበትም አንስተዋል።
የነገዋ የሴቶች ተሀድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር ልኬ ኃይለማርያም በበኩላቸው፤ በዛሬው የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ-ግብር ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ፀድቀው ለፍሬ እንዲበቁ በማዕከሉ ወስጥ የሚገኙ ሰልጣኞችን በማሳተፍ የመንከባከብ ሥራ እንደሚሰራ ገልፀዋል።
የማዕከሉ ግቢ በአረንጓዴ ልማት የሚታወቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዛሬው ችግኝ ተከላም ገጽታውን ይበልጥ የሚያጎላ ነው ብለዋል።
በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ከተሳተፉት ባለድርሻ አካላት መካከል የታፍ ኢነርጂ የቦርድ አባል የሆኑት ኤልሳቤጥ ፈታሂ፤ ድርጅቱ ለምግብነት የሚያገለግሉ የፓፓዬ፣ የአፕልና የአቮካዶ ችግኞችን በነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ግቢ መትከሉን ገልጸዋል፡፡
ችግኞቹ የተተከሉበት ቦታ ለመንከባከብ አመቺ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ችግኞችን እንደሚንከባከቡም ተናግረዋል፡፡
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የመርኃ-ግብሩ ተሳታፊዎች መካከል ዶክተር ፍስሃ ዋሱ እና እየሩሳሌም አንዷለም በአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ-ግብር ችግኞችን በመትከላቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
በነገዋ የሴቶች ተሀድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ችግኝ የተከለችው ሰልጣኝ እየሩሳሌም አንዷለም እንደገለጸችው፤ አረንጓዴ ዐሻራ ለመጪው ትውልድ ጉልህ ፋይዳ አለው።
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተተከሉት ችግኞች ለፍሬ እንዲበቁ እንክብካቤ እንደምታደርግ ነው የተናገረችው፡፡
ከታፍ ኢነርጂ የመጡት ዶክተር ፍስሃ ዋሱ በበኩላቸው፤ አረንጓዴ ዐሻራ ለትውልዱ ምቹና ሥነ-ምኅዳሯ የተጠበቀ ሀገር ለማስረከብ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
በዘንድሮ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱ ይታወቃል፡፡