በዞኑ ከ800 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመኸር አዝመራ እየለማ ይገኛል

አምቦ፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ በምዕራብ ሸዋ ዞን ከ800ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመኸር አዝመራ እየለማ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በዞኑ ወልመራ ወረዳ በዘንድሮው መኸር አዝመራ በኩታ ገጠም የሚለማ ገብስ ዘር ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተረፈ አራርሳ እንደገለጹት በመኸር እርሻው 889ሺህ ሄክታር መሬት በዘር የመሸፈን ስራ እየተከናወነ ነው።

በመኸር አዝመራው በቆሎ፣ ገብስ፣ ማሽላ እና ስንዴ በኩታ ገጠም የሚለማ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 60ሺህ 425 ሄክታር መሬት የሚሆነው በገብስ እንደሚለማ ተናግረዋል።

በእስካሁኑ ሂደትም ከታረሰው መሬት ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው በዘር መሸፈኑን ገልጸው ከግብዓት አንጻርም ምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች በስፋት እየቀረበ መሆኑን አብራርተዋል።

በምርት ዘመኑ የተሻለ ምርት ለማግኘት 9ሺህ 146 ሄክታር በአሲድ የተጠቃ መሬት በኖራ በማከም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የወልመራ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርናና መሬት አስተዳዳር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ደሳለኝ ተሾመ፤ የወረዳው አርሶ አደሮች የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴን እየተለማመዱ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ምርትና ምርታማነት እያደገ መምጣቱን ገልጸው በዘንድሮ መኸር እርሻ በወረዳው 32ሺህ 760 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በማልማት 2ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥም በወረዳው አራት ቀበሌዎች 5ሺህ 700 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በቢራ ገብስ የማልማት ስራ ተጀምሯል ብለዋል።

በወረዳው 9ሺህ አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም ተደራጅተው በአሲድ የተጠቃ መሬትን በኖራ በማከም የግብርና ልማቱን ውጤታማ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የወረዳው አርሶ አደሮች በበኩላቸው ገብስን በኩታ ገጠም ማልማት እምብዛም ያልተለመደ መሆኑን ገልጸው ዘንድሮ በወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት በተደረገላቸው ድጋፍ ገብስን በኩታ ገጠም በማልማት ምርታቸውን ለፋብሪካ ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

አርሶ አደር አሰፋ አንጋሱ፣ መሬታቻው በአሲድ የተጠቃ በመሆኑ የሚያገኙት ምርት አነስተኛ እንደነበረ በማንሳት ከግብርና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር መሬታቸውን በኖራ በማከም ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰሩ ነው።

ሌላው አርሶ አደር ሁንዴ ቶላ፤ በአሲድ የተጠቃ መሬታቸውን በኖራ አክመው የሰብል ምርታማነትን ማሳደግ ከጀመሩ ሶስት ዓመታት እንደሆናቸው አስታውሰዋል።

በዚህም የመሬቱ የአፈር ለምነት ወደ ቀድሞ ሁኔታው በመመለሱ በየዓመቱ የሚያገኙት ምርት እያደገ መምጣቱን ገልጸው ዘንድሮም ከገብስ ልማት ተጠቃሚ ለመሆን መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም