የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የአፈር መሸርሽርን በመከላከል ፅዱ እና የተሻላች ኢትዮጵያን ለመፍጠር እያገዘ ነው - ባለስልጣኑ

ሸገር፤ ሐምሌ 5/2017(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር የአፈር መሸርሽርን በመከላከል ጽዱ እና የተሻላች ኢትዮጵያን ለመፍጠር እያገዘ መሆኑን የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።

ባለስልጣኑ ከኦሮሚያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር በሸገር ከተማ ገላን ክፍለ ከተማ በአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሂደዋል።

በመርሃ ግብሩ የፌዴራል የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተሰራው ሥራ ፅዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ለሚከናወኑ ሥራዎች ጠንካራ መሰረት ጥለዋል ብለዋል።

በተያዘው ዓመትም የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሰባት ወራት የሚቆይ ጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ እያካሄደ መሆኑን አስታውሰዋል።


 

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር የአፈር መሸርሽርን በመከላከልና ምንጮች እንዲጎለብቱ በማድረግ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።

የተራቆተ የተፈጥሮ ሀብት መልሶ እንዲያገግም ከማድረግ ጎን ለጎን ጽዱና ጤናማ አካባቢን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አስረድተዋል።

በመሆኑም ባለስልጣኑ በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች እየተከለ መሆኑን ተናግረዋል።

በዛሬው እለትም ከኦሮሚያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን፣ ከሸገር ከተማ አስተዳደር እና ከግል ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት በገላን ክፍለ ከተማ የተካሄደው ችግኝ ተከላ የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን አስረድተዋል።


 

የኦሮሚያ ክልል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሴፋዲን ማሃዲ በበኩላቸው በክልሉ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር በተከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል።

የክልሉ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በአረንጓዴ ልማት ሥራ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸው፣ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ካለው ፋይዳ ባለፈ ለዜጎች የሥራ እድል መፍጠሪያ እየሆነ መምጣቱን አመልክተዋል።

ከመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ክበበው ሙሉነህ ችግኝ ለአካባቢ ውበትና ጽዳት ያለውን ሚና በመገንዘብ በየዓመቱ ችግኞችን በመትከል ዐሻራቸውን እያኖሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሌላው ተሳታፊ የሮን ተካልኝ በበኩላቸው ለሁሉም ምቹ  የሆነች ጽዱና አረንጓዴ ኢትዮጵያ መፍጠር የሚቻለው ዛሬ በሚተከሉ ችግኞች በመሆኑ ሁሉም በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ሊሳተፍ ይገባል ብለዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም